
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርእሰ መሥተዳደሩ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
ለመላው የሀገራችን እና የክልላችን ሕዝቦች፤
እንኳን ለ2014 የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!!!
ያለፈው 2013 ዓመት እንደሀገርም ሆነ እንደ ክልል በርካታ ተስፋዎች እና ፈተናዎች ያስተናገድንበት አመት ነበር።
ከመልካም አፈፃፀሞቻችን መሳ ለመሳ በርካታ ፈተናዎች የተጋፈጥንበት ዓመት ቢሆንም ፈተናዎችን በድል ለመወጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ በተሻለ ሀገራዊ አንድነት መንፈስ ተንቀሳቅሰናል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፤ የአማራን ሕዝብ ለማዋረድና አንገት ለማስደፋት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይልና ግብረአበሮቹ ጋር አንገት ለአንገት የተናነቅንበት፤ ሕዝባችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለህልውና ትግሉ ግንባር ቀደም ተሰላፊ በመሆን መስዋእትነት በመክፈል ሀገሩን ብሎም ማንነቱን ለማስጠበቅ በጀግንነት የተንቀሳቀሰበትና የተዋደቀበት ዓመት ነበር።
በዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ኀይል የተከፈተብንን የሽብር ጥቃት ለመመከትና ለማክሸፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳየው አንድነትና በፊት ተሰላፊ ግንባር ቀደም ተጠቂ ለሆነው የአማራ ሕዝብና ክልል በአስቸጋሪ ወቅት ላሳያችሁት አጋርነትና በመስዋእትነታችንና በደማችን ኢትዮጵያን ለማዳን ላደረግነው ትግል ከፍተኛ ምስጋናየን አቀርባለሁ።
የዘንድሮውን አዲስ ዓመት የምንቀበለውም በህልውና ትግል ውስጥ ሁነን አሸባሪውን ወራሪ እና ዘራፊ ኀይል በአማራ ክልል በወረራ በገባባቸው በሁሉም አካባቢዎች መቀበሪያው እንዲሆን እየታገልን በአንፃሩ ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ለማቋቋም ጥረት እያደረግን የምንቀበለው አዲስ ዓመት ነው።
የጀመርነው ፀረ ትህነግ ትግል የሚያበቃው ይህ ፀረ ኢትዮጵያ ፀረ አማራ ባንዳ ኀይል ለሀገራችን ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ስናደርሰው ብቻ መሆኑን አውቀን ለተጨማሪ ትግል ራሳችን ማዘጋጀት አለብን።
ስለሆነም የ2014 አዲስ ዓመትን ስንቀበል እንደተለመደው ሁሉ ሙሉ ቀልባችንና ስሜታችን የመንደራችንና የቀያችን የጎጇችን ድባብ እንደ አማራ ባሕል እንደ ኢትዮጵያውያን ወግ “በዓል በዓል” እንዳይሸት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በከፈተብን ግልጽ ወረራ እና ጭፍጨፋ የልብ ስብራታችንን ያስተናገድንበት ቢሆንም ኢትዮጵያዊና አማራዊ አንድነታችንን ከመቸውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ጠላቶቻችንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተን እብሪታቸውን የምናስተነፍስበት መሆኑንና ለተጨማሪ ትግል መላዉን ሕዝባችንን የምናሰልፍበት ወቅት ላይ ሆነን ነው።
በዚህ አጋጣሚ በዚህ ታሪካዊ ተጋድሎ ከፍተኛ ጀብዱ እየፈፀማችሁ ለምትገኙ፣ ሀገራችንን ከብተና ሕዝባችን ከውርደት ላዳናችሁ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ለሁሉም ክልሎች የልዩ ኀይል አባላት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ለአማራ ሚሊሻ ፣ ለአማራ ፋኖ እና በደጀንነት ታሪክ እየሠራችሁ ላላችሁ ለመላው የሀገራችንና የክልላችን ሕዝቦች ያለኝን ልባዊ አክብሮትና ምስጋና በእኔና በክልሉ መንግሥት ስም ለመግለፅ እወዳለሁ።
አዲሱ ዓመት ፈተናዎቻችን ሁሉ በድል ተሻግረን የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናይበት እንደሚሆን እምነቴ የፀና ነው።
መልካም አዲስ ዓመት!!
“ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!”