ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የ2014 የዘመን መለወጫ በዓል አስመልክቶ የተላለፈ መልዕክት፡-

120

ውድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣

አስቀድሜ፣ ይህንን የ2014 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ ሰላምታና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቴን በራሴና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስም ሳስተላለፍ ከፍ ያለ ክብርና ታላቅ ደስታ ይሰማኛል። አዲስ ዓመት በኢትዮጵያውያን መንፈስ የለውጥ መገለጫ እንደመሆኑ ከፀሐይ ብርሀን እና ከምንወዳት ኢትዮጵያ በቀለማት ያሸበረቀ መልክዓ ምድር ጋር ይመጣል። ይህም አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ ከፍ የምትሉበት፣ እንዲሁም በወንድማማችነትና በአንድነት የምትደምቁበት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡

ባለፈው ዓመት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ አሠራርና ሙሌት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ያለንን አንድነትና ቁርጠኝነት በሚያንጸባርቅ መልኩ አከናውነናል፡፡ ግድቡን በምንገነባበት ወቅትም በገንዘብም ይሁን በቴክኒክ ድጋፍ ሁላችንም የበኩላችንን በተሻለ ደረጃ ከማበርከት ወደኃላ አላልንም፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባደረጉት ርብርብ እጅግ ተደስታቸለሁ፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታትም የበለጠ አስደናቂ ውጤቶችን እንድንመዘግብ ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መደገፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አሳስባለሁ፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የህዳሴው ግድብ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የአሸናፊነት ነጥቦችን እንድናስመዘግብ የጎላ ሚና የተጫወቱትን ዲፕሎማቶቻችንና ከተለያዬ ዘርፍ የተውጣጡትን ባለሙያዎቻችንን ልናደንቃቸውና ልናመሰግናቸው ይገባል፡፡ እንዲሁም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች” የሚለውን እሳቤ ይዘን ባደረግናቸው ተከታታይ ውይይቶችና ድርድሮች በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የሚመራውን የድርድር ሂደት እውን ለማድረግ እና የህዳሴ ግድቡ የሦስትዮሽ ድርድር በመርሆዎች ስምምነት መሰረት እንዲሆን የተደረገውን ጥረት እናደንቃለን፡፡ ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ሙሌት ኢኮኖሚዊ እድገታችንን ለማነቃቃትና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ያነገብነውን የብልጽግና ተልእኮ ከግብ ለማድረስ አንድ ትልቅ ምዕራፍን የተሻገርንበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ያስመዘገብነውን ስኬት እያዬን ዋናውና የመጨረሻ ግባችንን መርሳት አይኖርብንም፡፡ ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን አስተውለን በተባበረ ክንድ የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

ያለፈው ዓመት ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጪ ተግዳሮችን በመቋቋም ጽናታቸውንና መንፈሰ-ጠንካራነታቸውን ከፍ አድርገው ያሳዩበት ዓመት ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ሕዝባችንን ከዳር እስከ ዳር ያስደነገጠው የጥቅምት 24ቱ የኢትዮጵያ ጠሉ ከሃዲ ቡድን የምሽት ጥቃት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ምልክትን ጥሎ ያለፈ ክስተት መሆኑን ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን አይረሱትም፡፡ በዚህ ደርዝ ባጣ ድፍረቱና ጨካኝ ድርጊቱ በሰሜን እዝ የነበሩ በርካታ ጀግና ወታደሮቻችንን አጥተናቸዋል፡፡ ያንን አሰቃቂ ሞት ከወታደሮቻችን አንዳቸውም አይገባቸውም። ይሁንና የሀገራችን ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ሕወሓት የተቃጡብንን ተግዳሮቶች በሚገባ በመመከትና ከጠላቶቻቸን በተቃርኖ የቆመ የተባበረ ሕዝባዊ ግንባርን በመፍጠር ጀግኖቻችን ለከፈሉት መሰዋእትነት አክብሮትን አሳይተናቸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን በወያኔ የተደቀኑብን ፈተናዎች ገና አላለቁም፡፡ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ያሉ ወገኖቻችን ከአሸባሪው ቡድን ቀንበር ነጻ መውጣታቸውንና ተፈናቃዮች ወደ የቀድሞ የመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችም ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ይህን ስናደርግ በእርግጠኝነት ቁስሎቻችን ይፈወሳሉ፡፡
በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ አረጋውያንን፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ግፍ እና ኢሰብዓዊ ግድያ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ እነዚህን ትርጉም የለሽ ግድያዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ሁሉም ሰላም ወዳድ የሆነ ሁሉ እንዲያወግዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ጠላቶቻችን እኛን ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነት ከመዳረጋቸው ባሻገር በኢኮኖሚያችንን ላይም መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍተውብናል፡፡ ሆኖም ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት እንዲያደናቅፉት በፍጹም መፍቀድ የለብንም፡፡ እነርሱ መሠረታዊ የፍጆታና ልዩ ልዩ የመገበያያ እቃዎችን በማከማቸት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ሕጋዊ ባልሆኑ መንገዶች በማስተላለፍ የልፋታችንን ፍሬ ሊያሳጡን የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ደባ ይበቃል የምንልበት ጊዜው አሁን ነው። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላሉ ወዳጅ ዘመዶች ገንዘብ በምትልኩበት ጊዜ በሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ተቋማት በመጠቀም ኢትዮጵያን እንድትደግፉ አሳስባለሁ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እውነትን ሰንቃችሁ ለሀገራችሁ ኢትዮጵያ በታማኝነት እና ሉዓላዊነትዋ እንዲከበር በጽናት ከጎናችን ለቆማችሁ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላትና መላው የኢትዮጵያ ወዳጆች ጥልቅ ምስጋናዬን ለመግለጽ እወዳለሁ።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣

በመካከለኛው ምሥራቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወገኖች እየደረሰባቸው ያለውን ችግር እንረዳለን። ለዚህም አስፈላጊውን እገዛ ከማድረግ ባለፈ፣ በሺዎች የሚቆጠሩትንም ወደ ሀገራቸው መመለሳችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ከስደተኞቹ ብዛት ጋር ተዳምሮ እርዳታ ለሚፈለጉ ዜጎቻችን ሁሉ ለመድረስ አቅማችንን ቢፈታተነውም በቻልነው ሁሉ ልክ እየተንቀሳቀስን ነዉ፡፡ በቀጣይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሠራ ቃል እገባለሁ፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

በርካቶች ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አቅማችንን ተጠራጥረውት የነበር ቢሆንም ለሰላም ጥልቅ ፍቅር ላለው ኢትዮጵያዊ ምስጋና ይግባና፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ያለማንም ከልካይነት፣ በነጻነት ድምጻቸውን የሰጡበትና ዐሻራ ያስቀመጡበት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ የምርጫው ውጤትም በአዲሱ ዓመት ወርሃ መስከረም መጨረሻ ልናቋቁመው ላለው አዲስ መንግሥት የኢትዮጵያውያን የማስተማመኛና የማስረገጫ ማህተሞች ናቸው፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ ብልጽግናንና ሕብረትን መርጠዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ እና ባለፉት ሦስት ዓመታት የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ ተሃድሶዎችን በማፋጠን የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን፡፡

በዘህ ወቅት ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን የማስተላልፈዉ ዋንኛ መልዕክት ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን በማድረግ እጅ ለአጅ እንድንያያዝና በአንድነት ጸንተን እንድንቆም ነዉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገራችን ዋና ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የተሃድሶ ሂደት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። እየተካሄደ ያለው ሪፎርም ለሀገራችን የበለፀገ የዲፕሎማሲ ታሪክ የሚመጥን ጠንካራና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሠራተኞችን ይፈጥራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር ሀገራቸውን እንደ አምባሳደር እንዲቆሙ ጥሪ አቀርባለሁ። ተሃድሶው በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን ዘርፎች የምንወዳትን ሀገራችንን ጥቅሞች ለመጠበቅ እና ለማስተዋወቅ ይረዳናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት ለሁላችሁም የሰላም፣ የጤና፣ የደስታና የብልጽግና ይሆንላችሁ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ፡፡
መልካም ዘመን፣
አመሰግናለሁ፡፡

Previous article❝ኢትዮጵያን የሚፈትኗት ኢትዮጵያን የማያውቋት ናቸው❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next article❝አዲሱን ዓመት ስናከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት መሆን ይገባዋል❞ ብፁዕ አቡነ አብርሃም