❝አላህ ይፍረደኝ የልጆቼን አባት አንገላተው ገደሉት፤ በወጉ ሳልቀብረው ጅብ አስበሉት ብጥስጣሽ ልብሱ ውርማ ተገኘ❞ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በወረባቦ ወረዳ በግፍ የትዳር አጋራቸውን የገደለባቸው እናት

219

ደሴ ፡ ጳጉሜን 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን መግደል ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻችንን አስክሬን ጅብ አስበልቶ የግፍ ግፍ ፈጽሞብናል ሲሉ የወረባቦ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በወረባቦ ወረዳ ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ አርሶአደሮችን በግፍ ገድሏል፤ ሃብትና ንብረት ዘርፏል ብሎም አውድሟል።

በወረባቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ካሊድ ሙሐመድ የተመራ ልዑክ አሸባሪው ትህነግ በወረዳው ጥቃት ያደረሰባቸውን፣ ንብረታቸው የተዘረፈባቸውንና የወደመባቸውን ወገኖች ተመልክቷል፡፡

በሰው ደም የሰከረው ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን በየደረሰበት ሁሉ የጥፋት ሰይፉን እየመዘዘ ንጹሐንን ገድሏል። ለአማራ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ በሚፈጽመው እኩይ ድርጊት እያሳየ ይገኛል።

በሁሉም ግንባሮች ከፍተኛ ሽንፈት ሲደርስበት ኀይሉን አሰባስቦ ደሴ፣ ሐይቅና ኮምቦልቻን መዳረሻዎቹ ሊያደርግ በደቡበ ወሎ በወረባቦ በኩል ጦርነት ከፍቶ የነበረው አሸባሪው ትህነግ የወረባቦ ወረዳን በወረረበት ወቅት ግለሰቦችን በግፍ ገድሏል፣ ንብረት ዘርፏል፤ አውድሟል።

ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ወረራ ከፈጸመባችው የወረባቦ ቀበሌዎች መካከል 018 ቁኖ ቀበሌ አንዱ ሲሆን ቡድኑ በዚህ ቀበሌ ንጹሐንን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን አሚኮ ከቦታው ድረስ በመሄድና የተጎጅ ቤተሰቦችን በማነጋገር አረጋግጧል።

ወይዘሮ ጦይባ ሙሐመድ የ4 ልጆች እናት ናቸው። የ30 ዓመት የትዳር አጋራቸው አሊ ዘገየ በአረም ሥራ ላይ እያሉ በግፍ ተገድለውባቸዋል። የሞቀ ጎጇቸውም አሸባሪ ቡድኑ በሐዘን አደፍርሶታል።

❝አላህ ይፍረደኝ የልጆቼን አባት አንገላተው ገደሉብኝ፤ ጌታ ይፍረደኝ በወጉ ሳልቀብር ጅብ አስበሉብኝ ብጥስጣሽ ልብሱ ውርማ ተገኘ❞ ብለዋል ሐዘን ባከሰለው ፊታቸው ላይ እንባ እየወረደ ።

ሌላኛዋ የተጎጅ ቤተሰብ ወይዘሮ አንሻ ሰይድ የ65 ዓመት እናታቸውን እንደገደሉባቸው ገልጸዋል። የእናታቸው አስክሬን በጅብ ተበልቶ ለምልክት ብቻ መገኘቱን ነው የገለጹት።

የሽብርተኛው የትህነግ ጀሌ የወገን ጦርን ብርቱ ክንድ መቋቋም ሲሳነው አፈሙዙን ወደ ንጹሐን አዙሮ እየጨፈጨፈ ከመፈርጠጡ ባሻገር የነዋሪዎችን ሀብት ዘርፏል፣ አውድሟል።

አሸባሪው ትህነግ በደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ ወረዳን በወረረበት ወቅት ንጹሐንን በግፍ ከመግደል ባለፈ፣ የአርሶ አደሮችን ቤትና ንብረት ዘርፏል፤ እንስሳትን ገድሏል። በማሳ ላይ የነበረ ያልደረሰ ሰብል ሳይቀር አውድሟል ነው ያሉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ካሊድ ሙሐመድ፡፡

በሽብር ቡድኑ የንብረት ዘረፋና ውድመት የተፈጸመባችው፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትና ከሞት የተረፉት ወገኖች ችግር ላይ በመሆናቸው ድጋፍን ይሻሉ ብለዋል።

ተጎጅዎችን የጎበኙት አቶ ካሊድ አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰዉ ጥፋት እንዳሳዘናቸዉ ገልጸዋል። ሕዝቡን በማስተባበር እንዲቋቋሙ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሰው ገድሎ የማይረካና አማራን ለማጥፋት የተነሳ በመሆኑ ሁሉም በአንድነት በመቆም ሊመክትና ቡድኑን ሊያጠፋ ይገባል።

ዘጋቢ:- ጀማል ይማም

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleከአማራ ክልል ምክር ቤት የዘመን መለወጫ በዓል አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አፈጉባዔ ወርቅሰሙ ማሞ የተላለፈ መልዕክት
Next article❝ኢትዮጵያን የሚፈትኗት ኢትዮጵያን የማያውቋት ናቸው❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ