
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፡- በሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ በጋረጠው አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ምክንያት ሕልውናችንን ለማስከበር ጦርነት ውስጥ ሆነን ወራሪው በተለያዩ አካባቢዎች በፈጠረው ጥቃት በሰው ሕይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱ ባሻገር በርካታ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው በተፈናቀሉበት ወቅት ሆነን አዲሱን ዓመት እየተቀበልን እንገኛለን፡፡
አሸባሪው ትህነግ በንጹሐን ላይ አደጋ እያደረሰ ቢሆንም በጀግኖች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በተባበረ ክንድ ኪሳራ እየደረሰበት ይገኛል፡፡ የህልውና ማስከበር ዘመቻችን የሚያበቃው ትህነግ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ ሲወገድና ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን ሲያረጋግጡ ብቻ በመሆኑ ባገኘናቸው ድሎች ሳንዘናጋ የጀመርነውን ትግል ማስቀጠል ይጠይቀናል፡፡ ወራሪው ትህነግ ኢትዮጵያን አፈርሳታለሁ ብሎ ቢነሳም የህልውና ጦርነቱ በመላ ሕዝባችን ድጋፍ የታጀበ በመሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከምንጊዜውም በላይ አንድ አደረገን እንጂ አልተሳካለትም፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአሰቃቂ ሁኔታ የንጹሐንን ደም አፍሷል፡፡ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አዛውንቶችና፣ የሃይማኖት አባቶች ለኢትዮጵያዊነት ሥነልቦና በማይመጥን መልኩ ተገድለዋል፣ ቤት ተዘግቶባቸው እንዲቃጠሉ አድርጓል፡፡ በነዚህ ንጹሀን ሞት፣ መፈናቀልና ስቃይ ምክር ቤታችን ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶታል፤ የኛን ህይወት ለማቆየት በክብር ለተሰው ለጀግናው የሀገር መከላከያችን፣ ልዩ ኀይላችን፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች ትግሉን የተቀላቀሉ የጸጥታ አካላት በየግንባሩ ደጀን ሆነው ለተዋደቁ ወጣቶችና ሴቶች ምክር ቤቱ ታላቅ ክብር የሚሰጠው ይሆናል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በመጨረሻም እንኳን ከ2013 ዓ.ም. ወደ 2014 ዓ.ም. አደረሰን እያልኩ መጭው ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የብሩህ ተስፋ ዘመን እንዲሆንልን እየተመኘሁ በዓሉን ስናከብር ለእያንዳንዳችን ህልውና ሲታገሉ ጉዳት ደርሶባቸው በየህክምና ተቋም የሚገኙ ወንድም እህቶችን እና ከቤታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን እያሰብን እንዲሆን እጠይቃለሁ፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!!