በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡

145
ጳጉሜን 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ዓላማ ኢትዮጵያን ማፈራረስና በዘረፈው ሀብትና ንብረት ትግራይን ገንጥሎ መውጣት እንደሆነ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና የጋይንት ግንባር የዘመቻ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ደሳለኝ ወዳጄ ተናግረዋል። ቡድኑ ባደረገው ወረራም በርካቶችን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ ሀብትና ንብረታቸውን ዘርፏል፣ አውድሟል ብለዋል።
አቶ ደሳለኝ ቡድኑ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችንም አውድሟል ነው ያሉት። ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሁሉ አርሶ አደሮች አረም እንዳያርሙና ማሳቸውን እንዳይንከባከቡ፣ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ሥራቸውን እንዳይሠሩ አድርጓል ብለዋል። ኅብረተሰቡ በምጣኔ ሀብቱ እንዲዳከም ማድረጉንም አስተባባሪው ጠቁመዋል።
የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ይዘርፋል የማይጠቅመውን ደግሞ ያወድማል ያቃጥላል ነው ያሉት። የአርሶ አደሮችን ከብቶች በጥይት ደብድቦ ገድሏል ብለዋል። “ቡድኑ ለሕዝብ መግለጽ የሚያስቸግርና አሳፋሪ የሆኑ ተግባራትን በሕዝቡ ላይ ፈጽሟል” ነው ያሉት።
አሁን ላይ ከወረራ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ በመረጋጋት የዕለት እንቅስቃሴውን እንዲቀጥልና በመደራጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ እየተሠራ እንደሆነም አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል። ያለምንም የመንግሥት ቅስቀሳ በየአካባቢው ያለው ኅብረተሰብ ሠፊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጤና፣ የቴሌ፣ የመብራትና ሌሎችም የወደሙ መሠረተ ልማቶች ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ መሆኑንም አስተባባሪው አመላክተዋል። የእነዚህ ተቋማት ቀና ትብብርና ርብርብ ወገንን የሚያኮራ እንደሆነም ገልጸዋል። በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ውድመት የሚያጠና ግብረኃይል መኖሩንም ጠቁመዋል። የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል ኅብረተሰቡ በትዕግሥት ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ግን ያላቋረጠ ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት።
“ጠላት ሁልጊዜም ጠላት ስለሆነ ኅብረተሰቡ በመደራጀት በአካባቢው የቀረውን የጠላት ቅሪት ሊለቅመው ይገባል” ብለዋል። ወጣቱ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ልዩ ኃይል ጎን በመሰለፍ ጠላትን በማጥፋት ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ ደሳለኝ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝አሸባሪው ቡድን እስካለ ድረስ ኢትዮጵያን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ ስለማይቦዝን ዳግም ሊያንሰራራ በማይችልበት መልኩ መደምሰስ እና ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ብቸኛው አማራጭ ነው❞ ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር
Next article“ለኢትዮጵያ የገባነውን ቃል ኪዳን አድሰንና አክብረን፣ የኢትዮጵያን ድል እናበሥራለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)