❝አሸባሪው ቡድን እስካለ ድረስ ኢትዮጵያን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ ስለማይቦዝን ዳግም ሊያንሰራራ በማይችልበት መልኩ መደምሰስ እና ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ብቸኛው አማራጭ ነው❞ ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

305
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የ2014 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው ያለፈው ዓመት እንደሀገርም ሆነ እንደክልል በርካታ ተስፋዎች እና ፈተናዎች ያለፉበት ነበር ብለዋል፤ ፈተናዎቹን በድል ተሻግሮ ተስፋዎቹ ላይ መሥራት የ2014 ዓ.ም የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
የ2014 አዲስ ዓመትን ስንቀበል እንደተለመደው ሁሉ ሙሉ ስሜታችን እንደ አማራ ባሕል እንደ ኢትዮጵያውያን ወግ እንዳይሆን አሸባሪው የትህነግ ቡድን በከፈተብን ግልጽ ወረራ እና ጭፍጨፋ የልብ ስብራቶችን አስተናግደናል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡ ፈተናዎቻችን በድል ተሻግረን የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከጥቅምት 29/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከማይካድራ እስከ ጭና፤ ከአጋምሳ እስከ ጋሊኮማ ኢትዮጵያ በርካታ የልብ ስብራቶችን አይታለች ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ሊነጋ ሲል ይጨልማልና የኢትዮጵያ ትንሣኤ እና የአማራ ዳግም ከፍታ በቅርባችን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከጥቅምት 24 የኢትዮጵያ መከዳት በኋላ አሸባሪው ቡድን ዳግም ወረራ በመፈጸም በአማራ እና አፋር ክልሎች ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን ፈጽሟል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው በዳግም ወረራው አሸባሪው ቡድን በገባባቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ሽዋ፣ ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ንጹሐን በግፍ ተገድለዋል፤ ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከመኖሪያ ቀየው ተፈናቃሏል፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ተጋልጧል፤ የመንግሥት የመሰረተ ልማት አውታሮች ፈርሰዋል፤ የግል ድርጅቶች እና የግለሰብ ሃብትና ንብረት ተዘርፏል ቀሪውም ወድሟል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ሁሉ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች ውስጥ ሆነን በምንቀበለው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ተስፋ ሰጭ የድል ብስራት ጀብዱ እየተፈጸመ መሆኑንም ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ አንስተዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም የአማራ ሕዝብ የሕልውና ስጋት እና የኢትዮጵያ አንድነት ነቀርሳ የሆነውን አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጦርነት ሲጀምር ሁለት ጊዜ እንዲያስብ በሚያስችል መልኩ እናስተምረዋለን ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን እስካለ ድረስ ኢትዮጵያን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ አይቦዝንም ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ዋናው መፍትሔ ዳግም ሊያንሰራራ በማይችልበት መልኩ መደምሰስ እና ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ብቸኛው አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም ክልሉን ከጦርነት ድባብ ለማውጣት ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል፡፡
አቶ አገኘሁ በሽብርተኛው ትህነግ በተፈጸመው ወረራ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታና ሥነ ልቦናቸውን መጠገን እና በጦርነቱ የታጣውን የግብርና ምርት በሚያካክስ መልኩ አተኩሮ መሥራት የክልሉ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም የፌዴራል መንግሥት፣ የተራድኦ ድርጅቶች እና ባለቤት የሆነው ሕዝብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ርእሰ መሥተዳድሩ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ በመልእክታቸው ጠላቶቻችን በከፍተኛ ርብርብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም ብለዋል፡፡ በፈተና ወቅት ከክልሉ ጎን ለቆሙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ክልሎች ምሥጋና አቅርበዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡
ተቋማት፣ የተራድኦ ድርጅቶች፣ ማኅበራት፣ አጋር አካላት እና ሕዝቡ ያደረጉትን ተጋድሎ ታሪክ አይዘነጋውም ብለዋል፡፡
በዓሉን እንደቀደመ ጊዜ በሙሉ ስሜት ለማክበር ወቅታዊ ፈተናዎች ቢበዙም ሁሉም ያለውን ተካፍሎና ማዕድ ተጋርቶ፣ በጦር ሜዳ ከጠላት ጋር እየተፋለሙ ላሉ ጀግኖች አጋርነትን በመግለጽ እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እንዲያሳልፍ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በዓሉን በሰላም ለማጠናቀቅ ሁሉም አጋር አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የጠየቁት ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ የክልሉ መንግሥት አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በርካታ የሕግ ታራሚዎችን በይቅርታ ይፈታል ብለዋል፡፡ ምሕረት የተደረገላቸው አካላት በሚደርሱበት አካባቢ ሁሉ የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይዎት እንዲመሩ ማኅበረሰቡ ቀና ትብብር እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ጭና ቀበሌ በፈጸመው ዘር ማጥፋት በተገደሉ ንፁሃን ዜጎች የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ።
Next articleበአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡