
የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈው ሙሉ መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል።
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ጭና ቀበሌ በፈጸመው ዘር ማጥፋት በተገደሉ ንፁሃን ዜጎች የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን።
አሸባሪው የህወሀት ጁንታ ንፁሃንን ማሸበር እና የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀም ዋና ተግባሩ አድርጎት ካሁን በፊት በአፋር ክልል ጋሊኮማ እና በተለያዩ አካባቢዎች እንዳደረገው በአማራ ክልልም በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ በርካታ ንፁሃንን ጨፍጭፏል።
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ በተለያዩ ግንባሮች ሽንፈትን እያስተናገደ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ንፁሃን ህፃናት፣ ሽማግሌዎችና ሴቶችን ሰለባ ያደረገ የዘር ማጥፋት በመፈፀም አረመኔያዊነቱን እና ኢ-ሰብዓዊነቱን በተደጋጋሚ በተለያዩ ቦታዎች እያሳየ ይገኛል፣ ይሄም በጭና ቀበሌ የተፈፀመው ጭፈጨፋ አንድኛው ነው።
በዚህ ጭፍጨፋ ውድ ህይወታቸውን በአሸባሪው ትህነግ ያጡ ንፁሃን ዜጎቻችን ትልቅ ሀዘን ተሰምቶናል፣ ሀዘናቹህ ሀዘናችን ነው፤ ንፁሃን በምንም አይነት መስፈርት ዒላማ ሊሆኑ አይገባም።
ይህ አይነቱ እኩይ ተግባር ለመቃወም እና ለማውገዝ ሰው መሆኑ ብቻ በቂ በመሆኑ በየትኛውም ጫፍ የሚገኝ የሰው ዘር በሙሉ ሊኮንነው ግድ ይላል። ንፁሃን ዜጎችን ዘርን መርጦ ጭፍጨፋ ማካሄድ የአረመኔት እና አውሬነት ጥግ ነው።
በመሆኑም ይህን ሰው በላ አውሬ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያችን ራስ ምታት የማይሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ግብዓተ መሬታቸው የግድ መፈፀም ስላለበት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ለአንድ ዓላማ በጋራ በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን አረመኔያዊ እና ኢ-ሰብዓዊ አስተሳሰብ መቅበር ግድ ይላል።
በመጨረሻም በጭፍጨፋው ህይወታቸውን ላጡ ንፁሃን ዜጎች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለአማራ ክልል ሕዝብና በጠቅላላ ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን እንመኛለን።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ጳጉሜን 04/2013
ሰመራ