
ሁመራ፡ ጳጉሜ 04/2013 (አሚኮ) ከሰላሳ ዓመት ግፍና ጭቆና በኋላ ከአሸባሪው የትህነግ አገዛዝ ነፃ የወጣችው የወልቃይት ጠገዴ ምድር ማንነቷን አስመልሳ እና ተጎናፅፋ በራሷ ባህልና ቋንቋ መጭውን አዲስ ዓመት ተቀብላ ለማክበር ሽር ጉድ እያለች ነው።
በጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ መስዋእትነት ወደ ቀድሞ ማንነቷ በጌ ምድር የተመለሰች ሲሆን ያገኘችውን ነፃነት ሳታስደፍር በልጆቿ አኩሪ ገድል ለወራት ሰላሟን አስጠብቃለች። “ይህ በዓል ነፃነታችንን አስመስክረን በነፃነት የምናከብረው ስለሆነ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ድርብ በዓላችን ነው” ያሉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው።
አቶ አሸተ ኀብረተሰቡ አካባቢውን በመጠበቅ እያሳየ ያለውን ተጋድሎ አድንቀው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወልቃይትን በቴሌቪዥን መስኮት ይሆናል እንጅ በአካል እመጣለሁ ካለ መቀበሪያው ይሆናል ነው ያሉት።
የዞኑ አስተዳዳሪ ኢትዮጵያ በታሪክ የገጠማትን የእናት ጡት ነካሽ ባንዳ አሸባሪ ቡድን እስከወዲያኛው ለማስወገድ ወጣቶች እያደረጉት ያለውን ተጋድሎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መጭውን አዲስ ዓመት ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት ለሌላቸው ያለንን በማካፈል ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ መዓድ በማጋራት ደጀን በመሆን እና የኢትዮጵያን ጠላቶች ድባቅ በመምታት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሁሉም የአማራ ሕዝብ አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ በአዲስ ተስፋ በአዲስ ጎዳና ለሀገራችን አንድነት ዘብ በመቆም በዓሉን ሊያከብር ይገባል ነው ያሉት፡፡ አቶ አሸተ መጭው ዘመን በተባበረ ክንድ ሀገር የምናቆምበት ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ – ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ