
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች አስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለማቅረብ ሁሉም እንዲረባረብ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ከ550 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ስለሚኖሩ በሴፍቲኔት ታቅፈው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የገለጹልን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ኢያሱ መስፍን የሽብርተኛው ትህነግ ወረራ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል፡፡ ለችግር ለተጋለጡ ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የአማራ ክልል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኢያሱ ኅብረተሰቡ፣ ባለሃብቱ፣ የልማት ድርጅቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ቀይ መስቀል ማኅበር እና ሌሎች አካላት በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ እና ችግር ላይ ላሉ ዜጎች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፉን ተደራሽነት ለማስፋት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ሌሎች የውጭ ሀገራት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተሳትፎ እንዲጨምር ውይይቶች መካሄዳቸውን የገለጹት ኀላፊው ወደ ተግባር እየገቡም ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለ377 ሺህ ዜጎች የዕለት ምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ የመስጠት ሥራ መጀመሩን እና ዩኤን ኦቻ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት 148 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መግባቱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ኢያሱ እንዳሉት የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን ወረራ በወረራቸው አካባቢዎች የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፡፡ በዚህም ነፍሰ ጡር እናቶች እና ጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሕክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም፤ በርካታ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መስተጓጎል ተፈጥሯል፤ እናም እነዚህን ተቋማት እና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት ኀላፊው፡፡
ዘጋቢ፡- ጥላሁን ወንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ