
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ_ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ተጋምደውና ተዋደው፣ ተደጋግፈውና ተዋሕደው የኖሩ ናቸው ብለዋል። የአብሮነት ቆይታቸው በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አመለካከትና በእምነት ያላቸውን የየራሳቸውን ማንነት ጠብቀው የቆዩ ሲሆን እንደ ሀገርም የጋራ ታሪክና እሴቶችን አዳብረዋል። የጋራ ስነ ልቦና እና ሕብረ ብሔራዊ ሀገራዊ እንድነት እየገነቡ ለዛሬ አድርሰዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን የየራሳቸው በሆኑ የማንነት ልዩ ልዩ መገለጫዎቻቸውና ጸጋዎቻቸው የሚያጌጡ፣ የጋራ በሆነው ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ደግሞ የህብር አንድነታቸውን ሲገልጡ ጠብቀው የኖሩ ህዝቦች ናቸው ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ሲመስሉ በአንድነት የሚተሙ፣ በጥላቻ ሊመሩዛቸው ሲሞክሩ ስለፍቅር በጋራ የሚዘምሩ፣ በሀገራቸውና በሉዓላዊነታቸው ጉዳይ ፈጽመው የማይደራደሩ ሕዝቦች ናቸው ብለዋል።
ለዚህም ዐይነተኛ ማሳያ ደግሞ አንዱ የአድዋ ድል መሆኑን የገለፁት ሲሆን በመሠረቱ ጣሊያን ወደ አድዋ ስትመጣ ተስፋ ያደረገችው ልዩነታችንን ተማምና እንደነበር በመግለፅ በልዩነታችን መካከልም ሰርጋ በመግባት የቅኝ ግዛት ቀምበሯን ልትጭኑብን ቋመጣ የነበረ ሲሆን በተለይም በዘመኑ አኩርፈው ቁርሾ ለነበራቸው የተወሠኑ ጥቅት ግለሰቦችን መደለያና ማባበያ በማቅረብ በባንዳነት ማሰለፍ፣ ቋንቋንና ብሔርን መሠረት በማድረግ አንዱን በአንዱ ላይ ጦር የሚያማዝዝ የሀሰት ትርክት መፍጠር እየሞከረች ቢሆንም ነገሮች ሁሉ እንዳሰበችው ሆኖ አላገኘችውም ብለው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሀገርን ሉዓላዊነት በአግባቡ የተረዱ በመሆናቸው “ቅድሚያ ለሀገር!” በማለት ከአራቱም ማዕዘናት ወደ አድዋ መትመማቸውን አስታውሰዋል።
በጀግኖቿ ተጋድሎም ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯን እና ሉአላዊነቷን አስከብራ ነጻ ሀገር ሆና በታሪክ ማማ ላይ ከፍ ብላ የታየች ስትሆን አድዋ ላይ የተለኮሰው የድል ችቦ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ቀንዲል ሆነላቸው ብለዋል።
ከድል በኋላ ላለው ኢትዮጵያዊ ትውልድም የአባቶቹ ገድልና ድል የነጻነትና የኩራት ምንጩ ሆኖ እንደቀጠለ የተነገሩት አፈ-ጉባዔው አሁን አገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው የአድዋ የነጻነት ትግል ዘመን ጋር የሚያመሳስላቸው በርካታ ነገሮች ያሉ ሲሆን የምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲካ ዛሬም እንደ ትናንቱ ተፈላጊነቱ እጅግ ያሻቀበበት ወቅት ላይ የምንገኝ ሲሆን ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መዳፍ ውስጥ አገራችን ለማስገባት የቋመጡ አከላት ያኔ አንዳንድ ግለሰቦች ለጣሊያን አድረው በባንዳነት ኢትዮጵያ አገራቸውን ለመውጋትና ለማዋረድም ከጣሩት ከሃዲዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ዛሬም አሸባሪዎቹ የሕወሀት ቡድንና ሸኔ በባንዳነት ሀገራችንን ለማዋረድና ሕዝባችንንም አንገት ለማስደፋት ደፋ ቀና ማለታቸውን አንዱ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንን ለመቀልበስና በአድዋ ላይ የተመዘገበውን ታሪክ ለመድገም ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድነት በመቆም የአገራቸውን ሉዓላዊነት በተባበረ ክንድ በማስከበር ላይ ይገኛሉ ፤ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን አጠናቀን ወደ ልማት መግባቱ ከእኛ አልፎ በኃይል እጥረት ለሚሰቃዩ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በዝቅተኛ ወጪ በቂ ኃይል እንዲያገኙ እናደርጋለን፤ በዚውም አብሮ የመልማትና የማደግ ሕልማችን እናሳካለን፡፡ የተላላኪ ባንዳዎችንም ቅስም ላይመለስ ሰብረን ሕብረ ብሔራዊ አገራዊ እንድነትን እናስቀጥላለን ብለዋል። የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ በማሳካት፤ ሠላምና የአገር አንድነት በማስጠበቅ ፤ የውስጥ የጥፋት ተላላኪዎችን በተባባረ የህዝቦች ተሳትፎ ተግባራቸውን በማምከንና እንደ አደዋ አባቶቻችን በአዲሱ ዓመት ድል እንቀናጃለን ማለታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
