“ቢከፋት ነው እንጅ በደሉ ቢመራት፣ ልጆቿን አስትቶ መታጠቅ ያማራት”

327
ደባርቅ፡ ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አዛኝ ናት አንጀቷ የሚላወስ፣ ደስታ ናት የፍቅር ሸማ የምታለብስ፣ የተከፋን አንጄት የምታርስ፣ መልካም ናት ለተራበ የምታጎርስ፣ እናትነት፣ መልካምነት፣ አዛኝነት፣ አርቆ አሳቢነት ሁሌም ከእርሷ ጋር ነው። ብልህ ናት ነገን የምታሰምር፣ ጠቢብ ናት ዘመንን የምታሳምር፣ የጀግና እናት ናት በጀግንነት የምትኖር።
ኢትዮጵያ ጀግኖችን እንድትወልድ የተመረጠች፣ በታሪክ የተከበረች፣ በዘመን የቀደመች፣ በምስጢር የተጠበቀች፣ መልካሙን የተሰጠች፣ የተሰጣትን የጠበቀች ሀገር ናት። ጀግና ትወልዳለች በጀግኖቿ ትጠበቃለች፣ ትከበራለች፣ ታሸንፋለች፣ ከፍም ብላ ትኖራለች። ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ቢበዙም የሚጠብቋት ኀያሎች ናቸውና በጠላቶቿ አትሸነፍም።
በቀደመው ዘመን ተፈትና አሸንፋለች፣ ዛሬም ታሸንፋለች፣ ነገም እንደ አሸነፈች ትቀጥላለች። ማሸነፍ ባሕሪዋ ነውና። በየዘመናቱ የተነሱባት ጠላቶች ተመተው ወደቁ፣ በምድሯ አለቁ፣ ያልደረሱት በዚያው ራቁ፣ ለክብር፣ ለምስክር፣ ለምስጢር ማስቀመጫ፣ ለክፉ ዘመን መወጣጫ የተመረጠችን ሀገር ማን ችሎ ያሸንፋል፣ ማንስ ችሎ ይጋፋል።
ከአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ፊት የሚቆም፣ የልጆቿን በትር የሚቋቋም ማንም የለም። የሠንደቁ ግርማ ረቂቅ ነው፣ የልጆቿ ክንድ ኀያል ነው። በኢትዮጵያ ጀግንነት ለወንድ ወይም ለሴት ተብሎ አይከፈልም። ሴቶቹም ወንዶችም ጀግኖች ናቸው። ሁሉም ሀገር ይመራሉ፣ ዘመን ያሳምራሉ፣ ጀብዱ ይሠራሉ፣ በጦር ሜዳ ጠላትን ድባቅ ይመታሉ፣ እየፎከሩ ምሽግ ይሠብራሉ፣ ለጠላት መብረቅ ይሆናሉ።
በሀገር ሲመጡባቸው ነብሮች ናቸው፣ ሴቶች በእናትነት አንጄታቸው ቢራሩም በኢትዮጵያ ከመጡባቸው አይታገሱም፣ ጠላት አይምሩም። ለዚያም ነው ጣይቱ ለሀገራቸው ሲሉ ሞትን ሳይፈሩ ጠላታቸውን ጦርነቱን እንዲያፈጥነው የጠየቁት፣ አሻፈረኝ ብለው የተነሱት፣ ወደ ዓድዋ የገሰገሱት፣ በብልሃታቸው የጦር ስልት የነደፉት፣ በነደፉት ስልት፣ በታጠቁት ጀግንነት፣ ከአባ ዳኘው ጋር በነበራቸው የተጣመረ ረቂቅ መሪነት ጠላታቸውን ድባቅ የመቱት፣ የአፍሪካን የጭቆና ዘመን የቋጩት፣ የኀያላን ነን ባዮችን አብዮት የበታተኑት፣ የሮምን ነገስታት አንገት ያስደፉት፣ የጥቁርን ዘር በሙሉ ያኮሩት፣ የጥቁርን ጀንበር ከፍ አድርገው ያበሩት።
አስተዋፆኦአቸው ይለያይ ይሆናል እንጅ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ጀግኖች ሴቶችን ከመውለድ አቋርጣ አታውቅም። የዘመኑ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ጠላት ትህነግ ሀገር ሊያፈርስ ሲነሳ ጀግኖች አይሆንም ብለው ተነሱ። ተው ብለው መከሩት አይሆንም ሲል ልኩን አሳዩት።
በማይጠብሪ ግንባር ተገኝቸአለሁ። ቆፈን ሳይበግራቸው፣ ብርድና ድካም ከዓላማቸው ሳያደናቅፋቸው በጽናት ከሚታገሉት ጋር ተገናኝቸአለሁ። ትጥቃቸውን አጥብቀው፣ ታላቅ ወኔ ሰንቀው ወደ ቆሙት ሴቶች ተጠጋሁ።
“ቢከፋት ነው እንጂ በደሉ ቢመራት
ልጆቿን አስትቶ መታጠቅ ያማራት” መከፋት፣ መገፋት አስነሳት፣ በመቀነት ፋንታ ጥይት እንድታዞርበት አስገደዳት። አብዝቶ የሚወደው አንጀቷ ቆረጠና በረሃ ወረደች። ከጠላት ጋር መዋደቅን መረጠች።
ታድላ ስማቸው ትባላለች። ሶስት ልጆች አሏት። የትህነግ አሸባሪ ቡድን በሕዝብ ላይ በደሎችን ሲፈጽም ተመልክታለች። በስልጣን ዘመኑ ሲያደርገው የነበረው ሁሉ ልቧን አድምቷታል፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጨምረው ክፋቱ አስቆጥቷታል። በዚህም ምክንያት በ2008 ዓ.ም ፋኖን ተቀላቀለች፣ አሸባሪውን ቡድንም መፋለም ጀመረች። እኔም ያገኘኋት የአሸባሪውን ትህነግ የመጨረሻ ቀብር ለመፈጸም ልጆቿን ትታ በማይጠብሪ ግንባር ተሰልፋ ነው።
“ አማራ ነኝ በማለቴ ብዙ ግፍና በደል ደርሶብኛል፣ ግፍና በደል ሲደርስብን ሰሚ የለንም ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ነው የምንታገለው እውነትን ይዘን፤ የምንታገለው ከአባቶቻችን የወረስነውን የሀገር ፍቅር ይዘን ነው። ፋኖ ማለት ከአያት ቅድመ አያት የተወረሰ የአባት ታሪክ ነው። የአባቶቻችንን ስም ይዘን ነው እየታገልን ያለነው” ነው ያለችኝ። ከአባትና ከእናት የወረሰችው አሸናፊነት፣ ከዘር የመጣው አትንኩኝ ባይነት ፊቷ ላይ ይነበባል። ልጅ ትታ በረሃ እንድትወርድ ያደረጋት በደል የከፋ መሆኑ ፊቷን አስተውሎ ላየ በቀላሉ ይረዳል። በደል እንዲያበቃ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በነፃነት እንዲኖሩ ነው የእርሷ መንገላታት።
“ ፋኖ ለአማራ ብሎም ለኢትዮጵያ የቆመ ነው” ብላናለች። ከልብ ጋር መምከር፣ ለነፃነት ፣ለአንድነት፣ ለክብር፣ ለሀገር ሲሉ የሞቀ ቤትን፣ የተመቻቸ ሕይወትን ትቶ ወደ ጦር ሜዳ መዝመት፣ ጠላትን መምታት፣ ሀገርን ነፃ ማውጣት ምን አይነት መታደል ነው። “ቤተሰቦቼ ወደ ፋኖ መግባቴን አያውቁም ነበር። ውስጥ ለውስጥ ነበር የምሠራው። ወደ ጦርነት ስገባ ግን ተይ አሉኝ። አይ እንግዲህ አባቴ ያስተማረኝ፣ ያወረሰኝ የሀገር ፍቅር ነው። ለሀገሬ መሞት አለብኝ። እኔ ሙቼ ለልጆቼ ወይም ለተተኪው ትውልድ ጥሩ ነገር ማቆዬትና ማሳዬት አለብኝ” አልኩ ነው ያለችው።
ቆራጥነቷ እየደነቀኝ፣ ጀግንነቷ እየገረመኝ ነው። “እኔ የሶስት ልጆች እናት ነኝ። ልጆቼን ከእናቴ ጋር ነው ጥያቸው የመጣሁት። እቅዴ ትህነግ የሚባል ቡድን ካልጠፋ አልመለሰም ነው። እንደ እኔ ላሉ ጓደኞቼ መልእክት የማስተላልፈው በዚህ ሰዓት ያልተነሳ ሴትም ሆነ ወንድ አማራም ኢትዮጵያዊም ነው ብዬ አላስብም፤ ሁሉም ኀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው” ብላኛለች። ትግል የሴት የወንድ አይልም የሀገር ጉዳይ ነው። አይደለም ወንድ ልጅ ሴት ልጅ ከቤት ውስጥ መቀመጥ የለባትም ነው ያለችው። እኛ አማራዎች ወደ ኃላ አንልምም ብላለች።
“ሴቶች ከቻሉ እንደ እኛ ገብተው ይታገሉ። በረሃ ወርደው ትግል መግባት ባይችሉ ስንቅና ትጥቅ ማቀበል አለባቸው” ነው ያለችው። አሸባሪው ትህነግን በተለያዩ ግንባሮች እየገባን እየመታነው ነውም ብላናለች። “አሽባሪው ትህነግ በጫረው ጉድጓድ እስከሚገባ ድረስ እስከመጨረሻው እታገለዋለሁ” የታድላ ቃል ነው።
ሌላኛዋ ፋኖ ደግሞ ብርቱካን ደስታው ትባላለች። እርሷም ዱር ቤቴ ብላ በረሃ ከወረደች ሰነባብታለች። ከጀግኖች ጋራ የጀግንነት ውሎ እየዋለች፣ የጀግንነት ታሪክ እየሠራች ነው። “ወራሪው እንዳሰበው አይደለም። ጥሩ አድርገን ተቀብለነዋል። አሳምረን መትተነዋል። ፋኖ አሸባሪው ትህነግ ጉድጓድ እስኪገባ ድረስ ይፋለማል። ሴቶች ቢችሉ እንደኛ ታጥቀው ቢገቡ፣ ካልሆነ ስንቅ ቢያቀርቡ ሌላ ትግል ነው” ብላለች።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ በዓይን ጥቅሻ እየተግባቡ ጠላትን እየደመሰሱ ወደፊት እየገሰገሱ ነው። ጠላት መውጫ ቀዳዳ ጠፍቶበት፣ ባሩድ በዝቶበት፣ የጀግኖች ክንድ አይሎበት እየፈረጠጠ ነው።
አዎ ኢትዮጵያ ዛሬም ትወልዳለች፣ ዛሬም በልጆቿ ትኮራለች። እንደተከበረች እንደ አሸነፈች ዘለዓለም ትኖራለች።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ለመግባት ውጊያ ቢከፍትም ሽንፈትን ተከናንቦ ተመልሷል” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰይድ መሐመድ
Next articleበሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለወገን ጦር የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።