በወሎ ግንባር የተሰለፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአሸባሪው እና ወራሪዉ የትህነግ ቡድን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሳቸው ተገለጸ።

229
ደሴ፡ ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ሕዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን እየገደለ፣ ንብረት እየዘረፈና መሰረተ ልማት እያወደመ ያለዉን የሽብር ቡድን ለማፈራረስና ከነአካቴዉ ለመቅበር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በየአቅጣጫዉ እየተፋለሙት ይገኛሉ፡፡
የመላዉ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጠላት የሆነዉን የትህነግ የሽብር ቡድን ለማፈራረስና ለመቅበር በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰሜን ፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክቶሬት ምክትል አዛዥ ኮማንደር ምትኩ ዳባ ገልጸዋል፡፡
በወሎ ግንባር የተሰለፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አሸባሪውን እና ወራሪውን ቡድን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡት መሆኑን ኮማንደር ምትኩ አስረድተዋል፡፡
አሽባሪዉ የትህነግ ቡድን በደረሰበት አካባቢ ጥፋት ፈጽሟል ያሉት ኮማንደር ምትኩ ቡድኑ በወረባቦ ወረዳ ጎሃ በተባለች አነስተኛ ከተማ ንብረት መዝረፉን እና ማውደሙን ነግረውናል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በከተማዋ ንጹሃንን በግፍ መግደሉንም ገልጸዋል፡፡ በጎኃ አካባቢ በተደረገ ዉጊያ የአሸባሪዉ ትህነግ ቡድን አዋጊ ጄኔራልን ጨምሮ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መገደላቸዉንም ነው ያረጋገጡት፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰሜን ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን አራት ፈጥኖ ደራሽ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ሀሰን አብዱ በበኩላቸው ወራሪዉ ቡድን ወደ አፋር ክልል እና ደቡብ ወሎ ዞን ሰርጎ ለመግባት ቢሞክርም የወገን ኀይል ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸዉን ቦታዎች በመያዝ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከአማራ ሚሊሻ እና ከፋኖ ጋር በመቀናጀት አኩሪ ድል እያስመዘገበ መሆኑንም አዛዦቹ አስታውቀዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግና ወራሪ ቡድኑን አሳዶ ለመደምሰስ እና መስዋእትነት ለመክፈል ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ዝግጁ መሆናቸዉን ኮማንደር ምትኩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር-ከወሎ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይልን በመቀላቀል ሀገርን ለማስከበር ዝግጁ መሆናቸውን የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
Next article“አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ለመግባት ውጊያ ቢከፍትም ሽንፈትን ተከናንቦ ተመልሷል” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰይድ መሐመድ