
ደብረ ታቦር፡ ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ዘቢጥ ግንባር አሸባሪውና ወራሪው የትህነግን ቡድን በመቅጣት ላይ የሚገኙ የአማራ ልዩ ኀይል የበላይ ዘለቀ ብርጌድ አባላት አዲሱን በዓል በድል እንደሚያከብሩ ለአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ገልጸዋል።
ረዳት ሳጂን ክንዱ ጌታቸው አሸባሪውና ወራሪው የትህነግን ቡድን ለማጥፋት ዝናብ፣ ፀሐይና ብርድ ሳይሉ እየተፋለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አዲሱ የዘመን መለወጫ በዓልን ሲያከብሩ ጠላትን በመደምሰስና በማጥፋት ስለሆነ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓሉ የሠላምና የደስታ እንዲሆንም ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

መቶ ዓለቃ ፍቅሩ ካሳ መላ ኢትዮጵያውያን አዲሱ የዘመን መለወጫ በዓል የሠላምና የደስታ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል። ለቤተሰቦቻቸውና ለትግል ጓዶቻቸውም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አድርሰዋል።
ኢንስፔክተር ፍቃዱ ከበደ የሽብር ቡድኑን በማጥፋት የተፈናቀለው የአማራ ሕዝብ ወደ ቀዬው ተመልሶ የተረጋጋ ሕይወቱን እንዲመራ እየታገሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። “አዲሱን የዘመን መለወጫ በዓል ሕዝቡን ከሽብር ቡድኑ በመጠበቅ በግንባር እናሳልፈዋለን” ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት በዓሉ የሠላም የደስታና የፍቅር እንዲሆንለት ተመኝተዋል። ሳጂን አስናቀ መንግሥት 2014 ዓ.ም የደስታና የድል እንዲሆን ተመኝተዋል። “አዲሱ ዓመት ጠላትን አጥፍተን በአዲስ ሕይወት፣ በአዲስ ራዕይ ወደ ሥራ የምንገባበት ዘመን ይሆናል” ብለዋል። ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ትህነግን እየቀጣነው ነው ብለዋል። አዲሱ የዘመን መለወጫ በዓል ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለትግል ጓዶቻቸው ሁሉ የድልና የፍቅር እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
ኮንስታብል ኤክራም እሸቱ በዓሉን ስታከብር ጠላትን በመደምሰስና ከጓዶቿ ጋር በመጨፈር እንደሚሆን ተናግራለች። “ዓላማችን ጠላትን መደምሰስ ስለሆነ በዓሉን ግንባር ላይ ማሳለፋችን ያስደስተናል” ነው ያለችው።

ታጋይ እሸቱ በርጃለው አዲሱ ዓመት አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያ የሚጸዳበት ዘመን ነው ብሏል። ጠላት እየተጨፈጨፈ ስለሆነ በደስታ የተሞላበት በዓልን እናሳልፋለን ነው ያለው። “በዓሉ ብቻ ሳይሆን ትግሉ በራሱ አስደሳች ነው፤ አሁን ላይ ጠላት የተበታተነ ስለሆነ በዓሉን በድል እንደምናሳልፍ እርግጠኛ ነኝ” ብሏል፡፡
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከኮኪት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ