በወልቃይት ጠገዴ ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ድል የተቀዳጁት የጸረ ሽምቅ ኀይል አባላት ጠላት ሳይጠፋ ወደቤታቸው ላይመለሱ ተማምለዋል።

173
ሁመራ፡ ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተሳሳተ ፖለቲካ ተጠቅሞ በሕዝብ መስዋእትነት ስልጣን የተቆናጠጠው ከሀዲ ቡድን መንግሥታዊ ሽብር ሲፈጽም ከቆየ በኋላ ለራሱ በሰጠው የተሳሳተ ግምት የማይደፈረውን ተንኩሶ የመጥፊያ ጊዜውን አሳጥሯል።
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደት ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በመንግሥት የተደራጀው ጸረ ሽምቅ ኀይል በጠላት ላይ ተደጋጋሚ ጀብድ ፈጽሟል። በአማራ ክልል መንግሥት ዕውቅና በሻምበል ደረጃ የተደራጀው ጸረ ሽምቅ ኀይል ዋንኛ ተልዕኮ የአካባቢውን ሰላም በንቃት መጠበቅ እና አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን እስኪወገድ መፋለም ነው።
የጸረ ሽምቅ ኀይል አባላቱ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ከፌዴራል እና ከክልል ሠላም አስከባሪ ኀይሎች ጋር በወሰዱት የተደራጀ የማጥቃት እርምጃ የጠላትን ምሽግ ደርምሰዋል፣ ወደ ሱዳኗ ሀምዳይት የፈረጠጡት የጠላት ታጣቂዎች በሁመራ ለመግባት ያደረጉትን ሙከራ በማክሸፍ አብዛኛውን ደምስሰዋል። የተወሰኑትን ምርኮኛ አድርገዋል፣ የግል እና የቡድን መሳሪያዎችን ከጠላት ማርከዋል።
ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮም ውጤታማ ኦፕሬሽን የሠራው ጸረ ሽምቅ ኀይሉ በአሁን ጊዜ በከፍተኛ ብቃት እና ቁርጠኝነት ጠላት ወልቃይት ጠገዴን ዳግም እንዳይረግጥ እየሠሩ ነው። በአጃቢነት እና ከተሞችን ተዘዋውሮ በመቃኘት ዞኑ በየትኛውም አቅጣጫ እንዳይደፈር እና ለጠላት እንቅስቃሴ እንዳያመች በማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። የጸረ ሽምቅ አባላቱ ክብራቸውን ለማስጠበቅ ቤታቸውን፣ ሀብትና ንብረታቸውን፣ ትዳር እና ቤተሰባቸውን እንዲሁም የግብርና ሥራቸውን በመተው በዓላማ ጽናት ትግል ከጀመሩ ዓመት ሊሞላቸው ነው።
“ሀገር ሰላም ሳትሆን ቤት ለምኔ ሀብትስ ምን ሊሆነኝ” በማለት ቁርጠኛ አቋም ይዘው አሁንም በጠንካራ የሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ናቸው። አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን ከገባበት ገብቶ ማጥፋት የመጨረሻ ግብ ያደረጉት የጸረ ሽምቅ አባላቱ “ኢትዮጵያን እና የሕዝቦቿን ህልውና የሚፈታተነው ባንዳ ሳይጠፋ ወደቤታችን አንመለስም” ብለዋል።
የዞኑ ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ምክትል ኀላፊ በላይ አያሌው እንዳሉት የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚቻለው የአማራ ሕዝብ የምን ጊዜም ጠላት የሆነው አሸባሪ ቡድን ሲጠፋ ብቻ ነው። ለዚህም ተጨማሪ የጸረ ሽምቅ ኀይል ማደራጀትና ስምሪት የመስጠት ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ከጠላት ጋር የመፋለም እና የውስጥ ባንዳን የማጽዳት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ በላይ ለዚህም ጸረ ሽምቅ ኀይሉን በብርጌድ ደረጃ የማደራጀት እሳቤ መኖሩን አመላክተዋል።
ወልቃይት ጠገዴ የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን የትኩረት ማዕከል ነው። ባለፉት ዓመታት ቡድኑ የራሱን አባላት ወደ ቦታው በማስፈር የአማራ ሕዝብን በማፈናቀሉ ከፍተኛ ትግል እየተደረገ ዓመታት አልፈዋል። ጠላት ከሕዝብ በመጣላቱ በስልጣን ላይ እያለ እንኳን ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል። የአማራ ሕዝብን ለማጥፋት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት እና ሀገር ለማፍረስ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወረራ የፈጸመውን አሸባሪ ቡድን የመፋለም ተግባሩ በመቀጠሉ ጠላት አሳፋሪ ሽንፈትን እየተከናነበ ነው።
የሰቲት ሁመራ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በሪሁን እያሱ ሕዝቡን የማንቃት፣ የማደራጀት፣ የማስታጠቅ እና የማሠማራት ተግባሩ ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል። አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን በአጭር ጊዜ ተረባርቦ በማጥፋት የትግራይን ሕዝብ ጭምር ነጻ በማውጣት ሂደቱ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የድረወሻውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታል ማውደም በጦር ወንጀልኝነት መታየት አለበት” አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ
Next articleሽብርተኛውን ትህነግ በማጥፋት ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዲመለስ እየተፋለሙ መሆኑን የአማራ ልዩ ኀይል በላይ ዘለቀ ብርጌድ አባላት ገለጹ፡፡