አሸባሪው የትህነግ ቡድን በከፈተው ወረራ በአማራ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚሹ ተገለጸ።

191
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል አራት ዞኖች በከፈተው ወረራ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያሻቸዋል ተብሏል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ከዓለም የምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ስቴቨን ኦማም ዎሬ ጋር ተወያይተዋል። አሸባሪው ቡድን በአማራ ክልል በከፈተው ወረራ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸው 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ይሻሉ ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ንጹሃንን በግፍ ገድሏል በርካቶችንም አፈናቅሏል ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ። ከዚህ በተጨማሪም መሰረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መውደማቸውን ገልጸው ለመልሶ ግንባታ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና ድርጅቶች ድጋፍ አሰፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
መጪው ጊዜ የትምህር ወቅት መጀመሪያ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ አውስተው በርካታ ትምህርት ቤቶች የሸባሪው ቡድን የጥቃት ሰለባ ሆነው ወድመዋል፤ የመሃል ሀገር አካባቢ ትምህርት ቤቶችም የተፈናቃዮች መጠለያ ሆነዋል ነው ያሉት።
የዓለም ምግብ ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የዓለም ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስቴቨን ኦማም ዎሬ (ዶክተር) የጉዳቱን መጠን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ገልጸው የሰብዓዊ ድጋፍ መቅረብ ጀምሯል ብለዋል።
በሰሜን ወሎ ዳውንት እና በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 14 ከባድ ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው ወደ አካባቢው እየደረሱ መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የችግሩን መጠን ተረድቶ ቅድሚያ ለመስጠት የተጣራ መረጃ ከክልል እና ከፌዴራል መንግሥት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ተወካዩ ድጋፉ በሚደርስባቸው አካባቢዎች የአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች እና ሕብረተሰቡ ቀና ትብብር እንዲያደርጉ ዶክተር ስቴቨን ኦማም ዎሬ ጥሪ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሠራዊቱ የአዲስ ዓመት መልዕክት።
Next article“ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታል ማውደም በጦር ወንጀልኝነት መታየት አለበት” አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ