
ደሴ፡ ጳጉሜን 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከራሱ በፊት የሕዝብ እና የሀገርን ክብር በማስቀደም ጋራ ሸንተረሩ ፣ ቁሩ እና ሀሩሩ ሳይበግረው አሸባሪውን ትህነግ በግንባር እየተፋለመ ይገኛል። በዚህም በአሸባሪው ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በማድረስ ድሎችን እያስመዘገበ ነው።
በወሎ ግንባር የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ለመከላከያ ሠራዊት አባላት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
ሜጄር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ባስተላለፉት የአዲስ ዓመት መልዕክት እንዳሉት ሠራዊቱ በሁሉም ግንባሮች አንፀባራቂ ድል እያስመዘገበ ይገኛል፤ ቁልፍ ቦታዎችንም ተቆጣጥሯል።
አዲሱ ዓመት ለመላው የሠራዊት አባላት እና ኢትዮጵያውያን የስኬት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ዓለሙ አየነ በጦርነቱ ከአሸባሪው ቡድን ይልቅ ተፈጥሮአዊ መልክዓ ምድሩ እና የአየር ንብረቱ እንደታገላቸው አንስተው ይሁን እንጂ ሠራዊቱ ከራስ በፊት ለሕዝብ እና ለሀገር ክብር ሲል ተልዕኮን በማስቀደሙ ከድል ላይ ድል እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ቡድን በሕዝቦች ላይ ያደረሰዉ በደል ሠራዊቱን በእልህ እና በቁጭት አነሳስቶ ለድል እንዲበቃ እንዳስቻለውም አንስዋል።
ሕዝቡ ከመጀመሪያዉ አንስቶ ከሠራዊቱ ጎን መቆሙን አንስተው ለሚያደርገዉ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። አዲሱ ዓመትም የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ዜና የሚሰማበት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።
ኮሎኔል ሁምኔሳ መርጋ አዲሱን ዓመት አስመልክተዉ ባስተላለፉት መልዕክት ለሁሉም የሠራዊት አባላትና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ “መልካም ዘመን ይሁንልን፤ እንኳን አደረሰን” ብለዋል። ዘመኑም የሠላምና የጤና፣ ጠላት ተደምስሶ የኢትትዮጵያ ሕዝብ እፎይታ የሚያገኝበት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ኮሎኔል መኳንንት ደሴ በበኩላቸው የደጀኑ ሕዝብ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል። ሕዝቡ ከደጀንነት ባለፈም ግንባር ድረስ ከሠራዊቱ ጋር እየተፋለመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“ለሕዝባችንም የድል ብሥራት እናበሥራለን፤ ሠራዊቱ በድል እንዲጓዝ ከፍተኛ አስተጽኦ እያደረገ ላለው ሕዝባችን እና ለሠራዊታችን እንኳን አደረሳችሁ፣ አደረሰን” ብለዋል። የድል ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ-ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ