❝ጧሪና ቀባሪ ልጃችንና የልጅ ልጃችን ገድሎብናል❞ አሸባሪው ትህነግ በዳባት ወረዳ ጭና አካባቢ ግፍ የፈፀመባቸው ነዋሪዎች

339
ደባርቅ: ጳጉሜን 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የማያበራ ግፍ፣ የማይቆም ሰቆቃ፣ የግፍ እንባ መፍሰስ፣ የእናት አንጀት ማላወስ። ደካማ ያለ ጧሪ፣ ቀባሪ መቅረት፣ ልጅ ከእናቷ መለዬት፣ ብዙዎች እናት እና አባት አልባ ሆነው ቀርተዋል፣ ብዙዎች ቤታቸውን ዘግተው ጠፍተዋል።
አሸባሪው ትህነግ እልፍ የአማራ እናቶችን ያለ ወግ ማዕረግ አስቀርቷል፣ አንጀታቸውን አድምቷል፣ እልፍ አባቶችን አሳዶ ገድሏል፣ ዛሬም ግፉ አልቆመም፣ ዛሬም የእናቶች እንባ አላባራም።
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ከሰሞኑ በዳባት ወረዳ ቆርጦ ለመግባት ባደረገው ሙከራ ድባቅ ተመቷል። አፈሙዝ የያዘውን አልችል ሲል ንጹሐንን እየጨፈጨፈ ነበር የፈረጠጠው። በወረዳው በወረራቸው ቀበሌዎች ብዙዎችን ገድሏል። ብዙዎችን ደፍሯል፣ ሀብት ንብረታቸውን ዘርፏል፣ አውድሟል።
በጭና ቀበሌ በደል ከፈፀመባቸው አዛውንቶች ጋር ተገናኝተናል። አቶ ባዜ ዘውዱ እና ወይዘሮ ገዳምነሽ መለሰ ይባላሉ። ሁለቱ ጥንዶች አቅማቸው ደክሞ ሮጦ መሥራት አቁመዋል። ይባስ ብሎ አቶ ባዜ ዓይናቸውን ታመው ማዬት ካቃታቸው አራት ዓመታት ተቆጥረዋል። ታዲያ ለደካማ ጉልበታቸው ምርኩዝ ይሆን ዘንድ ፈጣሪ ልጅና የልጅ ልጅ ሰጥቷቸው ነበር። ክፉ ነጠቃቸው እንጂ። ልጃቸው ካሕን ነበሩ። ቄስ ጥፍጥ በዜ ይባላሉ። በቤታቸው ያሳደጉት የልጅ ልጅ ሙሉቀን አኖረኝ የሚባል የልጅ ልጅ ነበራቸው።
በማዕረጋቸው መቀመጥ ሲገባቸው እያለቀሱ ነበር ያገኘናቸው። ሁለት የተበደሉ ነብሶች። ጧሪ ቀባሪ ያጡ አዛውንቶች። በአረጀ እድሜያቸው፣ በደከመ ዓይናቸው እንባቸውን እያፈሰሱ ተቀምጠዋል። ❝ወራሪ አፈነን፣ የጥይት በረዶ እየወረደብን መውጫ አጥተን ተቀመጥን። ልጄን ገደሉት፣ ያሳደኩትን የልጅ ልጄንም ገደሉት❞ ነበር ያሉን።
ምርኩዞቻቸው ተሰብረዋል፣ ብርሃኖቻቸው ጠፍተዋል፣ መሪዎቻቸው አልፈዋልና ሐዘናቸው ከባድ ነው። ፍዬልና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን አርደው እንደበሏቸውም ነግረውናል። ❝የልጅ ልጄ በቅበላ ተድሮ ዓለም ሳያይ ገደሉት፣ ጧሪዬን ተጠነኩ። የሚያርስልኝ፣ የሚንከባበከበኝ ልጄ ነበር አጣሁት❞ ነው ያሉት።
ወገናችን አልቋልም ብለውናል።
❝ሙሽራው ልጄን ገደለብኝ፣ ሳናስበው በጨለማ መጥተው ገደሉት። አይተው የማያምኑኝን ልጆቼን ገደሏቸው❞ ነው ያሉት።
የዳባት ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የጥናት ቡድኑ አባል ዲያቆን ሀብታሙ ስዩም አሸባሪውና ወራሪው ኃይል በወረራቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት አድርሷል ነው ያሉት። በወረዳው ዳግም ማይካድራ ፈፅሟልም ብለዋል። በተለይም በጭና ቀበሌ ቀሳውስትን፣ መነኮሳትን ገድሏል፣ ሕፃናትን ደፍሯል። በርካታ ሰዎችን ገድሏል ነው ያሉት። ቡድኑ ተመቶ ሲመለስ ንጹሐንን እየጨፈጨፈ መመለሱን ነው የተናገሩት። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፣ ደብዛቸው ያልተገኘ ሰዎችም አሉ ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ ንብረት ዘርፏል፣ አውድሟልም ነው ያሉት። ከቤትና ንብረት የተፈናቀሉትና ከሞት የተረፉት ወገኖች ችግር ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleቺርቤዋ ናሲ 30 ጌርክ 2013 ም.አ
Next articleየሠራዊቱ የአዲስ ዓመት መልዕክት።