❝አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ጠላቶች በአምሳያቸው ጠፍጥፈው ያበጁት ቡድን ነው❞ ዶክተር የሻምበል አጉማስ

281

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሌላን የማይሹ፣ የራሳቸውን የማያሸሹ ቢሆኑም ጠላቶቻቸው ግን ከዚህ በተቃራኒው የቆሙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጥንተ ጠላቶች በኢትዮጵያውያን ልዩ ባህል፣ ወግና እምነት ቅናት የተጠናወታቸው፣ በእምቅ የተፈጥሮ ሃብቷ አፍቅሮተ ንዋይ ያናወዛቸው እና በኢትዮጵያውያን ጀግንነት የሚበሳጩ ነበሩ፤ ናቸውም፡፡

ኢትዮጵያን ከዓድዋ እስከ ካራማራ፣ ከማይጨው እስከ መተማ፣ ከቀይ ባሕር እስከ ምስር ሊወጓት ከፈለጉ የጦር አረሮች ጀርባ ጥንተ ጠላቶቿ ስውር እጆቻቸው ረጅም እና ውስብስብ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ዓባይን የሚያህል ወንዟን አልምታ እና ከውኃው ተጎንጭታ ከጥሟ መርካት ስለምን ተስኗት ባጀች? የሚል አሰላሳይ ቢነሳ የትብታቡ ምንጮች “ነጮች” ናቸው ከሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡

ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለም ተነጥላ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተለይታ ስለምን ይህን ያክል ዘመን ግሉል ሆና ቆየች? ቢባልም የጥንተ ጠላቶቿ ስውር የሴራ እጆች ምላሽ ሆነው ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡

ተዘርቶ የማይበቅል የተቀቀለ ስንዴ ሰጥተው ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሃብቷን ያለቡ፤ መርፌ አውጠው ማረሻ ያስተፏት እና ብድር አበድረው ወኔ ለመስለብ የዳዳቸው የኢትዮጵያ ጥንተ ጠላቶች ዛሬም የአካሄድ ለውጥ አደረጉ እንጅ እርግፍ አድርገው እስከ ወዲያኛው አልተዋትም፡፡ ዛሬ ጉዳያቸውን ጉዳዬ ብሎ የሚያስፈጽም የጎረቤት ሰንኮፍ እና የውስጥ ሰነፍ ዘርተው ካበቀሉባት ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የካይሮ ፈረሶቹ ልዑክ እና የሌሎች ጋሻ ጃግሬ መልዕክተኛ የሆነው አሸባሪው የትህነግ ቡድን አንዱ ነው፡፡

አማራ ጠሉ እና የኢትዮጵያዊነት ዓይነ ጥላ የተጠናዎተው አሸባሪው ትህነግ ❝በዓለም ላይ የሚጠላትን ሀገር የመራ ምናልባትም የመጀመሪያው ድርጅት ሳይሆን አይቀርም❞ ብለዋል የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ በአንድ ወቅት፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ በሥልጣን ዘመኑ ሳይቀር ❝ከኢትዮጵያ ይልቅ ሱዳን ትሻለናለች፤ ኢትዮጵያዊነት የአድሃሪያኑ የክብር ካባ ነው፤ ባንዲራ ጨርቅ ነው❞ እና መሰል ነውሮችን ሳይሸማቀቁ በአደባባይ ሲደሰኩር በጆሮአችን ሰምተናል፤ በተግባርም የጥንት ኢትዮጵያውያን መለያ የሆኑትን ግብረ ገብነትን እና ታማኝነትን አሽቀንጥሮ ጥሎ በመሪዎች አንደበት እና በእንደራሴዎቻቸው ፊት ❝ሌብነት እስከአልተያዙ ድረስ ሥራ ነው❞ እስከማለት የደረሰ የማፍያ እና ጋጠወጥ ቡድኖች ስብስብ ነው፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለመናድ እና ሕዝቦቿን ለማዋረድ እስከ ሲኦል ለመውረድ የወሰነው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን የኢትዮጵያ ጥንተ ጠላት ብቻ ሳይሆን የጥንተ ጠላቶቿ ውላጅ ነው፡፡

❝አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ጠላቶች በአምሳያቸው ጠፍጥፈው ያበጁት ቡድን ነው❞ ያሉን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የአማራ ወጣቶች ማኅበር አባል የሻምበል አጉማስ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ ፊት ለፊት ተዋግተው ኢትዮጵያን ማሸነፍ ያልቻሉት ምዕራባውያን እንዲያውም ለአፍሪካ አህጉር ከቅኝ ግዛት ባርነት ነፃ መውጣት ምክንያት የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ነው ይላሉ ዶክተር የሻምበል፡፡

ዶክተር የሻምበል እንደሚሉት ከቀደመ ጥላቻቸው ጋር በኢትዮጵያ ምክንያት የአፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት ተዳምሮ በኢትዮጵያ ላይ ጥርስ የነከሱ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ሕልውናዋ እንዲጠፋ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡

ምዕራባውያኑ በሃይማኖት፣ በተራድኦ፣ በዲፕሎማሲ፣ በቱሪዝም እና በብሔር ፖለቲካ ስም የኢትዮጵያን ስብራቶች ለማብዛት ያለመታከት ለረጅም ጊዜ ሠርተዋል ባይ ናቸው፡፡ ❝የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውነት ስብራቶች ዘርፈ ብዙ እና ስር የሰደዱ ነበሩ❞ የሚሉት ዶክተር የሻምበል ሽብርተኛው ትህነግ የእነዚህ ስብራቶች ሁሉ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆኖ ብቅ ያለው ግን ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ምዕራባውያን እና ውላጆቻቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደ አማራጭ ከሚጠቀሙበት አንዱ አማራ ማጥፋት ነው፡፡ ይህን አካሄድ የሽብርተኛው ትህነግ አባላት ከምስረታቸው ጀምረው በማኒፌስቷቸው ያቀነቅኑት መሆኑን ያወሱት ዶክተር የሻምበል የሆነውም እየሆነ ያለውም ከኢትዮጵያ ጥንተ ጠላቶች የተቀዳ ነው ይላሉ፡፡ ምሁሩ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የኢትዮጵያ ጥንተ ጠላቶች ተላላኪ እና ጉዳይ አስፈፃሚ ሆኖ እየሠራ መሆኑን አንስተው አሁን ያለው አማራጭ ተላላኪዎችን እስከወዲያኛው መሸኘት ነው ይላሉ፡፡

❝ስብራቶቹን እያከከ እና እያስታመመ የሚኖር ትውልድ ከስብራቱ አይጠግግም❞ የሚሉት ዶክተር የሻምበል ይህ ትውልድ እንደ አባቶቹ ጠቢብ፣ አስተዋይ፣ በሳል፣ አሻጋሪ እና ጠላቶቹን አምርሮ የሚጠላ መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

ዶክተር የሻምበል እንዳሉት በቅርቡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በገባባቸው አካባቢዎች ማንነቱን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ❝አማራን እየገደለ እንዲቀጥል መፍቀድ አይገባም❞ ብለዋል፡፡

ራስን መሆን እና ወደ ራስ መመለስ የዚህ ትውልድ ትልቅ የቤት ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከተሠሩብን ሥራዎች መካከል በአንድ መቆም እንዳንችል ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

አማራ ❝መሪ ከፈጣሪ ይመረጣል❞ ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው የሚሉት ዶክተር የሻምበል መሪዎቻችን የቱንም ያክል ክፍተት ቢኖርባቸው እንኳን እርስ በርስ ጣት ከመቀሳሰር እና ከማብጠልጠል ወጥተን በአንድ መቆም ይገባል ብለዋል፡፡ ያኔ ከስብራቶቹ ያጠገገ አማራ እና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ የምናይበት ጊዜ ቅርብ ይሆናልም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የ 11 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next article❝መልካምነት በመስዋእትነታቸው ብዙ ለሆኑልን ለመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ቤተሰቦቻቸው❞ ዶክተር አሕመዲን መሐመድ