ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።

317

አዲስ አበባ: ጳጉሜን 02/2013ዓ.ም (አሚኮ) በጎ ፈቃደኛ የወሎ ተወላጆች ያዘጋጁት ይህ መርኃ ግብር አሸባሪው ትህነግ ሰሜን ወሎን በመውረር ያፈናቀላቸው ዜጎችን ለመርዳት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ስትራቴጅክ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዩሐንስ ቧያለው አሸባሪው የትህነግ ቡድን በርካታ የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን በመውረሩ ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በየትምህርት ቤቱ ተጠልሎ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የመጠለያ ጣቢያዎች የተጠለሉ ወገኖች እንደሚኖሩ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ እንግዳ ተቀባዩ የደሴ ሕዝብ እያገዛቸው ቢሆንም ቁጥሩ የበዛ በመሆኑ መተጋገዝ ግዴታ ሆኗል ነው ያሉት። ”ከዚህ በፊት አማራ በተፈናቀለ ቁጥር እየጠየቅናችሁ ነው፤ ይሁን እና አሁንም ሳትሰለቹ ከችግሩ ስፋት አንጻር መደገፍ አለባችሁ“ ሲሉ ለባለሃብቶች ጥሪ አቅርበዋል።

የሕዝብ እንደራሴ አባል ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ በየቦታው ተፈናቅለው የሚገኙት ወገኖች እጅጉን የሚያሳዝን ሁኔታ ላይ በመሆናቸው መደጋገፍ ይገባል ብለዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ኡስታዝ ሙሐመድ አሕመድ “የሚበላው ያለው ለሌለው ማሰብ አለበት፤ ከዚህ የባሰ ዘመን አይገጥመንም እና አንረዳዳ ”ብለዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መደገፍ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000430217578 ወይም በዳሽን ባንክ ሂሳብ ቁጥር 5444260316011 መርዳት እንደሚችሉ ነው የተገለጸው፡፡

አሸባሪው ትህነግ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች በፈጸመው ወረራ ከ500 ሺህ በላይ አማራዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ችግር ውስጥ እንደወደቁ መገለጹ የሚታወስ ነው።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“አረመኔውና ጨፍጫፊው ትህነግ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ተክለኃይማኖት ቀበሌ በርካታ ንፁሃንን ጨፍጭፏል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
Next articleኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ወጥተው በሱዳን መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ስደተኞች በጦርነት መሳተፋቸውን ገለጸ።