
ደብረታቦር: ጳጉሜን 02/2013ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የደብረ ዘቢጥ ከተማ ነዋሪዎች የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ግፍ በቁርጠኝነት ከወገን ኀይል ጎን ተሰልፈው እንዲታገሉ እንዳደረጋቸው ለአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ተናግረዋል።
መለሰ አሰፌ የተባሉት ነዋሪ ወራሪው ቡድን በድንገት ወረራ ቢፈጽምም የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር ሲፋለሙ እንደነበረ ተናግረዋል። ከዚህ በኋላም ጠላትን ለመልቀም ዝግጁ እንደሆኑ ነው የተናገሩት። አሁን ላይ በግንባር ለተሰለፉ የወገን ኀይሎች ደጀን እየሆኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
መኩሪያው አበበ የተባሉት ሌላው ነዋሪ ጠላት ከአካባቢው እንዲጠፋ ለወገን ኀይል የስንቅና የመረጃ ድጋፍ ሲሰጡ እንደቆዩ አስረድተዋል። “ከእንግዲህ ጠላት ወደ ከተማችን ከሚገባ ሞታችንን እንመርጣለን” ብለዋል። አሁን ላይ ርዝራዡን የጠላት ቅሪት እያጸዱ እንደሆነም ተናግረዋል። በወረራው ወቅት ጠላት ያላቸውን ሁሉ ቢዘርፍም ባላቸው አቅም ለወገን ኀይል ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል።
ወጣት መላኩ ተሾመ ጠላት ሳያስቡት በድንገት ከተማቸውን እንደወረረው ተናግረዋል። የከተማዋ ወጣቶች አሁን ላይ ጠላትን ለመደምሰስ ከወገን ሠራዊት ጋር ተሰልፈው እየተፋለሙ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ መኮንን “የጠላትን ዓላማና ተልዕኮ በተግባር ስላየን በቁርጠኝነት ለመታገል ዝግጁ” ነን ብለዋል። ሀገርን ለሚታደግ የወገን ኀይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለውን ድጋፍ እንዲያደርግም ወይዘሮዋ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከኮኪት ከተማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ