“አሸባሪውና ወራሪውን የትህነግ ቡድን አጥፍቶ የሕዝብን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሰልጥኖ እና ታጥቆ መሰለፍ ያስፈልጋል” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

323
ሁመራ: ጳጉሜን 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ የአማራ ልዩ ኀይል ምልምል ሰልጣኞችን ወደ ማሰልጠኛ ልኳል። በመርኃግብሩ የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እንዳሉት ውትድርና ከምንም በላይ የተከበረ ሙያ ነው፤ ሀገርን ለማስከበር ወታደር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ውትድርና ፈተናዎችን በቀላሉ ለማለፍ፣ በመልካም ሥነ ምግባር ለመታነጽ፣ በፍቅር አብሮ ለመኖር፣ ነጻነትን ለማስጠበቅ፣ ጠንካራ አካላዊ እና ሥነልቦናዊ አቅም ለመገንባት፣ የኢትዮጵያን ጥንካሬ አንድነት እና ሕብረት ለመገንባት የሚጫወተው ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ወታደር የሌለው ሀገር መዝጊያ እንደሌለው ቤት ይቆጠራል፣ ጠንካራ ወታደር ያለው ሀገር ደግሞ ሉዓላዊነቱን ያስጠብቃል ነው ያሉት፡፡
ኮሎኔል ደመቀ እንዳሉት ወጣቶች በቁርጠኝነት ተሰልፈው ሕዝባቸውን ከጥቃት ኢትዮጵያንም ከውርደት የሚታደጉ የመጨረሻ ምሽግ ናቸው። ትናንት አማራነት እንዳይነሳ፣ የኢትዮጵያዊነት እሳቤም እንዳይቀነቀን የአማራ ሕዝብን ሲያጠፋ የነበረውን ወራሪ ቡድን አጥፍቶ የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሰልጥኖ እና ታጥቆ መሰለፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን በመስጠት ሀገርን ለማስከበር ቆርጠው የተነሱና ልዩ ኀይሉን የተቀላቀሉ ምልምል ሰልጣኞች ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
ምልምል የልዩ ኀይል አባላቱ ሲሰባሰቡ የጠንካራ አማራ ምሳሌ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል። አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን እስከመጨረሻ ተከታትሎ የማጥፋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡ ልዩ ኀይሉን ለማጠናከር የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ወጣቶች በስልጠና ቦታ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በብቃት አልፈው ለሕዝባቸው የሚመጥን ቁመና በመገንባት የክልሉ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ መከታ እንዲሆኑም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከውስጥ ተሰግስገው የተለያዩ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ የጠላት አባላት ሊኖሩ ስለሚችሉ በንቃት መከታተልና መንጥሮ ማውጣት ከሰልጣኞች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሚሰጣቸውን ስልጠና በንቃት ተከታትለው በዲሲፕሊን የታነጸ ብቁ ወታደር በመሆን ለማንኛውም ግዳጅ መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው ኮሎኔል ደመቀ መልእክት ያስተላለፉት።
የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አማረ ጎሹ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ገናና ያሰኛት የስልጣኔ ባለቤት መሆኗ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ የተለያዩ ሥርዓተ መንግሥቶችን ያስተናገደች የጀግንነት ቀንዲል እንደሆነችም ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሀገሪቱ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የሕዝብን ስልጣን ይዞ ሀገር ለመበዝበዝ የሠራ ብቸኛ ስብስብ ነው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ባለታሪክ ነው፣ የሚሞተውም ሆነ መስዋእትነት የሚከፍለው ኢትዮጵያን ለማዳን እና አማራን ከውርደት ለመታደግ ነው ብለዋል። ለዚህም ዳር ድንበር ሳይገድበን ለዓላማ የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። “በወያኔ ሥርዓት በወልቃይት ጠገዴ ምድር ኮማንደር፣ ኮሎኔል፣ጀኔራል፣ ኮሚሽነር የሚባል የለንም፣ የእኛ የወደፊት ኮማንደር፣ ጀኔራል፣ ኮሎኔል እና ኮሚሽነሮች እናንተ ናችሁ፤ እዛ ለመድረስ በጠንካራ የዓላማ ጽናት ልትሠሩ ይገባል” ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለማዳን እና የአማራን ሕዝብ ከመጥፋት ለመታደግ ጠላትን ከገባበት ገብቶ ማጥፋት ከምልምል የልዩ ኀይል አባላት ይጠበቃል ነው ያሉት።
አሚኮ ያነጋገራቸው ምልምል የልዩ ኀይል አባላት የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና በአግባቡ በመከታተል በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚቃጣ ምንኛውንም ጥቃት በብቃት ለመመከት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የልዩ ኀይል አባል በመሆናቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ጠቅሰዋል።
አሸባሪውን ትህነግ ከገባበት ገብተው እስከመጨረሻው ለማጥፋት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – ከዳንሻ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበእስራኤል ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለህልውና ዘመቻው ከ14 ሽህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next articleበስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ29 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡