ለአፋር ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ሕዝባዊ ሠራዊት እንዲሁም ለአፋር ተፈናቃይ ወገኖች የ150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ።

210
አዲስ አበባ፡ ጳጉሜን 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተለያዩ ባለሀብቶች አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሀገርን ለማፍረስ በአፋር ክልል ያደረገውን ወረራ በመመከት ላይ ለሚገኘው የአፋር ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ሕዝባዊ ሠራዊት እንዲሁም ለተፈናቃይ ወገኖች የ150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉንም ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል።
የአፋር ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኀላፊ አቶ ሙሀመድ ሀሰን እንደገለጹት የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በፀጥታ ኀይሉ እየተደመሰሰና ወደ መጣበት እየተመለሰ ነው፤ በወረራውም ከ150 ሺህ በላይ ዜጎችን አፈናቅሏል፡፡ ኀላፊው ይህ ጉዳይ የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ድጋፍ ላደረጉ ባለሀብቶች ምሥጋና አቅርበዋል።
ባለሀብቱ አቶ አበባው ደስታ የአማራ ባለሀብቶች፣ የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌዴራል መንግሥትና የአፋር ክልል መንግሥት ያደረገውን የድጋፍ ጥሪ በመቀበል በተደራጀ መልኩ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አበባው በመስዋዕትነት የተቀበልናትን ሀገር ለጠላቶች አሳልፈን አንሰጥም፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ክብርና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አንደራደርም ብለዋል። አፋር ለኢትዮጵያ ጉሮሮ መሆኑን እና ይህንንም በተግባር ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ይህንን መደገፍ ስለሚገባም የአማራ ባለሀብቶች 50 ሚሊዮን እንዲሁም በአፋር ክልል በኢንቨስትመንት የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች 50 ሚሊዮን በድምሩ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
አቶ ወርቁ አይተነው በግላቸው 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ሌላኛው ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ እንዳሉት የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ሀገርን ለማፍረስ ዝግጅት አድርጎ ወደጦርነት ገብቷል። ሕዝቡን በዘረኝነት እሳቤው ቀስቅሶ በአፋርና አማራ ክልል ላይ ጦርነት ከፍቷል። ኢትዮጵያ ያለፍላጎቷ የገባችበትን ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል።
አቶ በላይነህ ክንዴ እንዳሉት የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነት የከፈተው በኢትጵያዊነቱ በማይደራደሩት የአሊ ሚራህ ልጆች በአፋሮችና በእነምኒልክ፣ በላይ ዘለቀ፣ አፄ ቴዎድሮስ ልጆች በሆኑት አማራ ላይ ነው፡፡ ይህንን ወረራ ተባብረን በድል እንወጣዋለን፤ እኛም ድጋፋችን ይቀጥላል ነው ያሉት።
አቶ ወርቁ አይተነው በአፋር ግምባር ላለው የመከላከያ ሠራዊትም የሰንጋ ግዢ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የአፋር ሕዝብ እየከፈለልን ስላለው መስዋእትነት እናመሥግናለን ብለዋል።
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የተመኘውን የጅቡቲ መስመር የመያዝ ህልምም በአፋሮች ከሽፏል ነው ያሉት። የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በዳማ ጨዋታ ሲመጣ አፋሮች በድል መልሳችኋልም ብለዋል። አስገራሚ የጦርነት ስልት አሳይታችኋልም ነው ያሉት አቶ ወርቁ አይተነው በግላቸው 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleከመስከረም 3 እስከ 15 /2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ በዓለም አቀፍ እና በሀገር ውስጥ የተጣመሩ ሴራዎችን ለማክሸፍ ሀገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።
Next articleበአጣዬ ከተማ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ቤታቸው ለተቃጠለባቸው 64 አባውራዎች የመኖሪያ ቤት ርክክብ ተደረገላቸው።