
ሁመራ: ጳጉሜን 02/2013ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው ትህነግ ለዓመታት ተጨቁኖ የነበረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጠላቱን ለመደመሰስ ዕድል አግኝቷል። አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ጽንሰቱ፣ ውልደቱም ሆነ እድገቱ በተንኮል የተተበተበ መሆኑ አሳፋሪ ውድቀት እንዲከናነብ አድርጎታል።
መዋቅራዊ ሽብር እየፈጸመ ሀገርን ሲበዘብዝ የነበረው የባንዳ ስብስብ ኢትዮጵያን ከክብሯ ዝቅ ሊያደርግ፣ ታሪኳን ሊያጠፋ፣ የሕዝቦቿን ሥነልቦና ሰልቦ አንገት ሊያስደፋ ብዙ ጥሯል። ብኩርናውን በመሸጥ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሳንባ የሚተነፍሰው ይህ የከሀዲዎች ቡድን ሀገሪቱን በድሎ ሕዝቦቿን ለባርነት ሲዳርግ የአማራ ሕዝብን በተለየ መልኩ በድሏል።
የሀገሪቱን ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ ለዓመታት የጎመጀበትን የወልቃይት ጠገዴ መሬት ከፖለቲካ እና ከሕግ አግባብ ውጪ በእጁ አስገብቶ የራሴ የሚለውን ሕዝብ ሲያሰፍር የአማራ ሕዝብ ግን መራራ መስዋእትነት እንዲከፍል ፈርዶበታል። በዚህ ምክንያት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በትህነግ እና በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ መካከል የተከፈተው ጦርነት ሀገራዊ ይዘትን ተላብሶ ትህነግን ከመንግሥትነት ወደ ሽፍትነት ቀይሯል።
በሕዝብ ትግል ከቤተ መንግሥት የተባረረው አሸባሪ ቡድን ከሞት አፋፍ ቆሞ እንኳን ለአማራ ሕዝብ ያለውን ጥላቻ በማይካድራው ጭፍጨፋ አሳይቷል። ከማይካድራው ጭፍጨፋ አምልጠው በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው በረከት ከተማ የሸሹትን አማራዎች እየተከተለ በጥይት እና መርዝ በተበከለ ውኃ እንደገደላቸው የዓይን እማኞች ተናግረዋል። በዚህም በርካቶች የተገደሉ ሲሆን 120 የሚሆኑ ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ሲፈጽም የከተማዋ ነዋሪዎች አንገታቸውን ደፉ፣ መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ድረስም አምርረው አዘኑ። ለረጅም ዓመታት ከተፈጸመባቸው ግፍ ጋር ተዳምሮ አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ እስከመጨረሻው ለመፋለም ቁርጠኛ አቋም ያዙ።
በረከት በኢትዮ-ሱዳን ወሰን ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። ማይካድራ ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ የፈጸመው ቡድን በዚች ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ሰፍሮ ወታደራዊ ስልጠና እያደረገ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። የጠላትን አሰላለፍ ጠንቅቆ የሚያውቀው የወልቃይት ሕዝብ እድል ቢያገኝ በባርነት እንኳን እንደማያኖረው ተገንዝቧል። ለዚህም እንቅስቃሴውን በንቃት እየተከታተለ ይገኛል፣ በጠላት ላይ የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድም እየተዘጋጀ ነው።
ለዘመናት ተጨቁኖ የነበረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በሀገር ወዳድ ጀግኖች ትግል ነጻ በመውጣቱ ጠላቱን ለመደምሰስ ዕድል አግኝቷል። ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት፣ ስንቅ በማዘጋጀት እና በጸጥታ ሥራው በመሳተፍ ውጤታማ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። ጠላት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴ እግር በእግር እየተከታተሉ ሙከራዎቹን እያከሸፉ እንደሆነ የከተማዋ ምክትል አስተዳዳሪ ወርቁ ገሰሰው ጠቅሰዋል።
ቀጣይ ጠላት ምንም አይነት ሙከራ እንዳያደርግ አስተማማኝ አቅም መገንባቱን ተናግረዋል። የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላትም የተቀናጀ ሥራ እየሠሩ ነው።
ኢትዮጵያውያን በነቂስ የሕልውና ዘመቻ በሚገኙበት ወሳኝ ምዕራፍ ፖለቲካዊ ስልትን በአግባቡ መጠቀም የአፈሙዝ ትግሉን ስኬት ስለሚያጎናጽፍ ፖለቲካውን በጥበብ መምራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ሕዝብን መስለው ለጠላት የሚሠሩ አካላትን መንጥሮ ማውጣትም ተገቢ ነው ብለዋል። የወገን ጦር በተገቢው መንገድ እንዲደራጅ ድጋፍ ማድረግ እና የልማት ሥራውን ማስቀጠልም የትግሉ አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
በወልቃይት ጠገዴ የተጀመረው ትግል አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን መከላከያን አጥቅቶ ሀገር ሊያፈርስ ከተንቀሳቀሰ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ተቀጣጥሎ ጠላት አሳፋሪ ሽንፈት ደርሶበታል። አሁንም ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት ነው የሚገኘው።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ