በመተማ ወረዳ ሽንፋና ጉባይ የውጊያ ግንባር የትግራይ ወራሪ ቡድን ከፍተኛ ሰባዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረሰበት ብርጋዴር ጄኔራል ናስር አባዲጋ ገለጹ።

729
መተማ: ጳጉሜን 02/2013ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ሽንፋና ጉባይ ግንባር ዛሬም ድሉና ጀብዱ እንደቀጠለ ነው። በክንደ ነበልባሉ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ የጠላት ጦር ባልጠበቀው ቅጽበት የሀፍረትና የውርደት ካባን እየተከናነበ ይገኛል።
ቀጣናውን የማተራመስ ህልሙ ቅዠት የሆነበትና መፈናፈኛ አጥቶ በርሃብ የደቀቀውን የሽብር ቡድን በመደምሰስና እጅ በመስጠት ላይ ይገኛል።
ከሱዳን በእነ ጄኔራል ፍስሃ ማንጁስ እስከ ቲሀ የተሸኘውና በቅማንት ጽንፈኛ ቡድን መሪነት ሽንፋና አካባቢው የገባው የአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ ቁሳዊና ሰባዊ ኪሳራ እንደደረሰበት የ8ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ናስር አባዲጋ ገልጸዋል።
በውጊያው ከ50 በላይ ክላሽ፣ 150 የዲሽቃ ጥይት፣ 500 የብሬል ጥይት፣ 1ሺህ የክላሽ ጥይት፣ 5 ጸረ ተሽከርካሪ ፈንጂ፣ 5 መገናኛ ራዲዮ፣ 3 አርቪዥና ቅንቡላ፣ ለምግብነት የሚያገለግል በዓይነት ብዛት ያለው መድኃኒት ከሽብር ቡድኑ መማረካቸውን ነው ጄኔራሉ የተናገሩት።
በዛሬው የውጊያ ውሎ 8 የሽብር ቡድኑ ምርኮኛ ተይዘዋል ያሉት ጄኔራሉ በየጫካው ወድቆ ያልተቆጠረውን፣ በአርሶ አደሩ እርምጃ የሞተውን እና ውኃ የወሰደውን ሳይጨምር ከ250 በላይ የሽብር ቡድኑ መደምሰሱን ገልጸዋል።
በሽንፋ ግንባር ያገኘናቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በካሀዲው ጄኔራል ፍስሃ ማንጁስ ሱዳን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲሰለጥን የቆየው የወያኔ ቡድን በቲሀ ገብቶ ቱመት፣ ሌንጫ፣ ጉባይ፣ ሽንፋና ለምለም ተራራ ገብቶ የሽንፋን ከተማ ለመቆጣጠር ቢሞክርም አልተሳካለትም ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ በሽንፋ የገባበት ዋና ዓላማ የቅማንትን ሕዝብ ደጀን አድርጎ በጭልጋ ወጥቶ ጎንደርን ለመቆጣጠር እንደሆነ አቶ ደሳለኝ የገለጹት።
አሁንም ቢሆን ሱዳን ውስጥ በእነ ጄኔራል ፍስሃ ማንጁስ፣ በእነ ኮሎኔል ተስፋዬ፣ በእነ ኮሎኔል እውነቱ እና በእነ መቶ አለቃ ገብረ ማርያም የሚሰለጥን ቡድን እንዳለ መረጃው ደርሶናል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።
እኔ ከሞትሁ ኢትዮጵያ ትፍረስ በማለት የጥፋት ተልዕኮውን ሰንቆ የሚንቀሳቀሰው የአሸባሪው ቡድን በእኛ ዘመን ንጹሃን ዜጎችን ሲገል፣ ሲደፍርና ሲያፈናቅል ማየት ሀፍረትና ውርደት ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደ አዋጊ ጄኔራል፣ እንደ ተዋጊ ወታደርና እንደ ሞተራይዝድ መሪ ግንባር በመሰለፍ እየተዋጉ መሆናቸውን ገልጸውልናል።
ዋና አስተዳዳሪው ደጄን የሆነው የዞኑ ማኅበረሰብ ከመከላከያና ልዩ ኀይል ጎን በመሰለፍ እያደረገ ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መርኮኞቹ እንዳሉት ከጥቅምት 24 በኋላ የትግራይ ወጣቶች እንግሊዝ ጀርመን ፈረንሳይ እና ካናዳ እንደሚላኩ እና ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሰጣቸው ከሱዳን በነ ጄኔራል ፍስሃ ማንጁስ ቅስቀሳ ተደርጓል፤ ወጣቶቹ ሱዳን ካርቱም ከገቡ በኋላም በሱዳን ወታደርና ፖሊስ ታግተው ወደ ስደተኞች መጠለያ ካንፕ መግባታቸውን ምርኮኞቹ ተናግረዋል።
ከሕዳር 13 ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ወራት ወታደራዊ ስልጠና እንደተሳጣቸው የተናገሩት ምርኮኞቹ ኢትዮጵያ የምትባለውን አፍርሶ ታላቋ ትግራይ እንድትመሰረት እንደሚደረግም ነው የገለጹት፤ የሽብር ተልዕኮ እንድንፈጽምም አስታጥቀው ጦርነት አስገብተውናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ -ከሽንፋ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ከዚህ በኋላ እኛም ከብቶቻችንም ተመልሰን ወደ ባርነት አንገባም” በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ እንስሳት አርቢዎች
Next articleበ34ኛ ዙር የብርሸለቆ መሰረታዊ ወታደሮች ምረቃ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ልዑካቸው ተገኝተዋል፡፡