
ሁመራ: ጳጉሜን 02/2013ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ምድር የእንስሳት እርባታ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲወራረስ የቆየ ባሕል ነው። ቆላማ የአየር ጠባይ ያለው የወልቃይት ምድር ለእንስሳት እርባታ እጅጉን ያመቻል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ከጥንት ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያለው እንስሳት የማርባት ልምድ አላቸው። በተለይ ከወያኔ ዘመን በፊት ያለምንም እንከን እርሻን ከእንስሳት እርባታ ጋር አሰናስለው በዘርፉ ተጠቃሚ ነበሩ።
ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወደ አካባቢው እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ግን ዘርፉ ፈተና ገጥሞታል። ማንነትን መሠረት አድርጎ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት እንስሳትም ለእንግልት ተዳርገዋል። እንስሳት የሚያረቡ ሰዎች እየታደኑ ወከባ ሲደርስባቸው በከብቶች ላይም የተደራጀ ዘረፋ ተፈጽሟል።

አማራዎችን በማፈናቀል የትግራይ ተወላጆች ዘርፉን እንዲቆጣጠሩት በማድረግም የኢኮኖሚ አሻጥር ሠርተዋል፣ በዚህም እንስሳት ሳይቀር ሽብርተኛው ቡድን ወደማይንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች መሰደድ ግዴታቸው ሆኖ በስደት ዓመታትን አሳልፈዋል።
በእርሻና በእንስሳት እርባታ የተሰማሩት ነጋ ባንቲሁን በደረሰባቸው ፖለቲካዊ ጫና አካባቢውን ጥለው ለሰባት ዓመታት ሲሸሹ ከብቶቻቸውንም ወደ ምዕራብ አርማጭሆ እና አብርሃጅራ አሽሽተው መቆየት የመጨረሻ አማራጫቸው ሆኗል። በዚህም የአካባቢውን ጸጋ ተጠቅመው ትልቅ የኢኮኖሚ መሠረት ከሆነው እንስሳት ሀብታቸው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም።
በመራር ትግል የተገኘውን ነጻነት ተከትሎ ግን ባለሀብቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች የእንስሳት እርባታን እንደ አዲስ እየጀመሩ ይገኛሉ። ከሰባት ዓመታት በኋላ አቶ ነጋ ወደ እርስታቸው እንስሳቱም ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡

ከዚህ በኋላ እኛም ከብቶቻችንም ወደ ባርነት ተመልሰን አንገባም ያሉት አቶ ነጋ ሥራው ወደፊት በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ዘርፉን ሰፊ የሀብት ምንጭ ለማድረግ በዕቅድ እንደሚሠራም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ከጎናችን እስካለ ድረስ ሰርተን ከመለወጥ የሚያግደን የለም በማለትም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
በዘርፉ የተሰማሩት ሌላኛው ባለሀብት በላይ ታደለም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል። ወልቃይት ለእንስሳት እርባታ ምቹ ቢሆንም ፖለቲካዊ ሁኔታው በፈጠረው ተጽዕኖ ከወተት እና ከስጋ ሀብቱ ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም። አቶ በላይ ከእንስሳት ሀብቱ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ ወደ ውጪ ሀገራት እስከመላክ ሀሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
እረኞች ከእንስሳት የሚግባቡበት የራሳቸው ቋንቋ አላቸው፡፡ በቦታው ተገኝተን እንደታዘብነው እንስሳቱ የእረኞችን ድምጽ በመስማትና ጠረናቸውን በማነፍነፍ ብቻ የሚለዩበት የተለየ ተፈጥሯዊ ባሕሪ አላቸው። ከሚግባባቸው ውጪ ማንም ሰው ደፍሮ መጠጋት፣ ወተት ማለብም ሆነ ወደፈለገበት መንዳት አይችልም፣ ለመግባባትም ቅድሚያ በእረኛ በኩል መተዋወቅ የግድ ይለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – ከቃብትያ ሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ