የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሜካናይዝድ ክፍል ጠላትን በመቅጣት አይተኬ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የደብረ ዘቢጥ ግንባር ጀግኖችና መሪዎች ተናገሩ፡፡

348
ሰሜን ወሎ ኮኪት፡ ጳጉሜን 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውና ወራሪውን የትህነግ ቡድን ድራሹን በማጥፋት ከእግረኛው ሠራዊት በተጨማሪ የሜካናይዝድ ኃይሉ አይተኬ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል። የ33ኛ ክፍለ ጦር 4ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አዛዥ ከጋሳይ ጀምሮ ጠላትን እየደመሰሰ ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ኮኪት ከተማ ደርሷል።
የሜካናይዝዱ የሥራ ኃላፊዎች ሜካናይዝዱ ከጋሳይ ጀምሮ በጠላት ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዳደረሰበት ተናግረዋል። ሜካናይዝዱ ጠላትን ባለበት እንዲደመሰስ አድርጓል ብለዋል። ጠላት መሽጎበት የነበረውን የደብረ ዘቢጥ ተራራ ሜካናይዝዱ ምሽጉን በማፈራረስ እዚያው እንዲቀር አድርጓል ነው ያሉት።
“የኅብረተሰባችንን ደኅንነት መጠበቅ ግዴታችን ስለሆነ ሁሉም ዒላማችን ጠላት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው” ብለዋል። መድፍ ተኳሽ የሆነችው የ33ኛ ክፍለ ጦር 4ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ መሠረታዊ ወታደር አዱኛ መሌ የጠላት ምሽግ ማፈራረስ፣ ከባድ መሳሪያዎቹን ማምከን፣ ካምፖቹን ማቃጠል፣ ምሽጎቹን ማፈራረስና መደምሰስ ችለናል ብላለች። በሜካናይዝዱ እያንዳንዱ ዒላማ ጠላት ላይ ያተኮረ ነው ብላለች። መድፍ ተኳሿ በጠላት ላይ ለተገኘው ድል የአስተኳሻችን ሚና ከፍተኛ ነው ብላለች።
ጠላትን ለመደምሰስ ሌት ከቀን በትጋት እየሠሩ እንደሆነ መድፍ ተኳሿ አስረድታለች።
የ33ኛ ክፍለ ጦር 4ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አሽከርካሪ ሻለቃ ባሻ ጌታ ካሳዬ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመንቀሳቀስ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድንን እየደመሰሱ እንደሆነ ተናግረዋል። የዝናብ ወቅት ቢሆንም ሜካናይዝዱ ያለውን ችግር ተቋቁሞ ጠላትን መደምሰስ ችሏል ብለዋል።
ሌላው መድፍ ተኳሽ መሰረታዊ ወታደር ልባሴ አበባው የደብረ ዘቢጥ ተራራ ለእግረኛው ሠራዊት አስቸጋሪ ስለነበረ ጠላትን ከስፍራው ለማላቀቅ ሜካናይዝዱ ግዳጁን በስኬት ተወጥቷል ብሏል። “በሚሰጠን ዒላማና ተልዕኮ ያለምንም ስህተት እንመታለን” ብሏል። “ጠላት እንዳናጠቃው በማሰብ በነዳጅ ዲፖ፣ በእምነት ተቋማትና በመሠረተ ልማቶች ስር ቢመሽግም ጠላትን ነጥለን በማለም መምታትና ማጥፋት ችለናል” ብሏል።
የደብረ ዘቢጥ ግንባር የሜካናይዝድ ክፍል አስተባባሪ እንዳሉት ደብረ ዘቢጥ ተራራ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም የሰለጠነና የወገንን ጉዳት በሚቀንስ መልኩ ጠላትን ቀጥቅጠን ደምስሰነዋል። የሜካናይዝድ ክፍሉ ጠላት አንገቱን እንዲደፋ አድርጓል ነው ያሉት። የሜካናይዝድ ክፍሉ የወገንን ጉዳት የሚቀንስ ጠላትን ደግሞ የሚያዋርድ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ጠላት እየተፍረከረከና እየተበተነ ነውም ብለዋል። ልዩ ኃይሉና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ አንድ ሆነው ጀብድ ያለው ሥራ እየሠሩ ነው ብለዋል። ጠላት ሁሌ የትግራይን ሕዝብ የማዋረድ ሥራ እየፈጸመ ነው ብለዋል። የሜካናይዝድ ክፍሉ መሠረተ ልማቶች እንዳይጎዱ በጥንቃቄ እየሠራ፣ ሁሉም ነገር በዘመነና በስሌት የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከኮኪት ከተማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleብርሸለቆ መሠረታዊ የውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ34ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ወታደሮች ዛሬ ያስመርቃል።
Next article“ልዩ ኀይሉ አሸባሪውን ቡድን እየደመሠሠ ወደፊት እየገሰገሰ ነው” የአማራ ልዩ ኀይል አባላት