“በ2014 ዓ.ም ችግሮቻችንን በመነጋገር በጋራ መፍታት እንጀምራለን፤ ነገር ግን መደማመጥ፣ ኅላፊነትን እና ግዴታን መቀበል ብሎም በጋራ መሥራትን መርህ ማድረግ ይኖርብናል” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ

305

ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ወጣቶች ማኅበር “ምክክረ አበርክቶ ለድል” በሚል መሪ ሐሳብ ከአማራ ክልል የመንግሥት ሠራተኛ ተወካዮች ጋር በባሕር ዳር ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ “ለዘመቻ ወቅት፣ ለድል ማግስት እና ለባሻገር” በሚል ርእስ የተዘጋጀ የመወያያ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶ.ር) ሀገሪቱ የገጠማትን የህልውና ፈተና በብቃት ለማለፍ በጋራ መቆም የግድ የሚለን ወቅት ላይ ነን ብለዋል፡፡ ለሀገራችን ከሚኖረን የግል አበርክቶ በፊት ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ራስን መሆን፣ መደማመጥ እና ሥርዓትን እና መሪን ማክበር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዘመናት በጥንተ ጠላቶቻችን ከተሠሩብን ድብቅ ሴራዎች መካከል አንዱ እንዳንደማመጥ ማድረግ ነው ያሉት ኅላፊዋ ክፍተቶች ቢኖሩ እንኳን በጋራ መሙላት እንጅ ጣት መቀሳሰር ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም ችግሮቻችንን በመነጋገር በጋራ መፍታት እንጀምራለን፤ ነገር ግን መደማመጥ፣ ኅላፊነትን እና ግዴታን መቀበል ብሎም በጋራ መሥራትን መርህ ማድረግ ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ “ለዘመቻ ወቅት፣ ለድል ማግስት እና ለባሻገር” በሚል ርእስ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ኮሌጅ መምህር ዶክተር የሻምበል አጉማስ ባለፉት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ መዋቅራዊ ስብራቶች ተፈጥረውበታል ብለዋል፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ባህላዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ስብራቶቹን በመጠገን ትውልዱን ከገባበት ችግር ለማውጣት ወቅቱ ዛሬ ነው ብለዋል ዶክተር አጉማስ፡፡ ተመሳሳይ ምክክሮች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንደቀረቡ የገለጹት ዶክተር አጉማስ የምክክር መድረኮቹ ዓላማ “የሕልውና ዘመቻውን በድል አጠናቀን በባለጠጋዋ ሀገር ምጡቅ፣ ገናና፣ ሃያል እና የታፈረ ትውልድ ለመገንባት” ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሕልውና ዘመቻው በድል መጠናቀቁ አይቀርም፤ ነገር ግን ሌሎች ስብራቶች እንዳይገጥሙን መነጋገር እና አቅዶ መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ነጋዴዎች ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኃይል፣ ለሚሊሻና ፋኖ የምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next articleብርሸለቆ መሠረታዊ የውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ34ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ወታደሮች ዛሬ ያስመርቃል።