
ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመስቀል ደመራ በዓል ከትናንት ጀምሮ ተከብሯል። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚድያ አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሠረት ላቀ ለአብመድ እንደተናገሩት በዓሉ በሠላም ሊጠናቀቅ የቻለው የሃይማኖቱ ተከታዮች፣ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በጋራ ባደረጉት አስተዋጽኦ ነው።
በተለይ በአብዛኛዎቹ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ከትናንት ጀምሮ በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ነው ምክትል ኮማንደሩ የገለጹት። ወጣቶቹ ከፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሆን ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖርና ወንጀል እንዳይፈጠር በማስተባበር ላሳዩት መልካም ተግባርም ምሥጋና አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ