የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን እና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከ71 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለተፈናቀሉ ወገኖች እና አሸባሪውን የትህነግ ቡድን እየተፋለሙ ላሉ የጸጥታ አካላት ድጋፍ አደረጉ፡፡

175

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን እና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ያደረጉት ድጋፍ ሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን በፈጸመው ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እና አሸባሪውን የትህነግ ቡድን እየተፋለሙ ላሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ድጋፉን ያደረጉት መሥሪያ ቤቶች ከተጣለባቸው ኀላፊነት በተጨማሪ ሀገር ከገባችበት ችግር እንድትወጣ ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ሀገር ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ መረዳዳት እና መደጋገፍ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ 60 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነት እና ቀሪው 11 ሚሊዮን ብር በጥሬ መሆኑን ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እያደረጉት ላለው ተከታታይ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ወረራ ለመቀልበስ የተቋማቱ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ “ሽብርተኛው ቡድን እየተቀበረ ነው፤ አስተሳሰቡንም በመቅበር በቅርቡ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን” ብለዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ ብቻ ሳይሆን የቅማንት ፅንፈኛ ተላላኪም እየተደመሰሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ አገኘሁ “የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመጨረሻዋን ሳቅ ይስቃሉ፤ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ደግሞ እስትንፋሱን ያቆማል፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ ነፃነቷ ይረጋገጣል፤ የሽብርተኛው ቡድን የመጨረሻ መቀበሪያው በአማራ ክልል እንደሚሆንም ነው” የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአሸባሪው የትህነግ ቡድን በወሎ ግንባር ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት ነው” ብርጋዴር ጀኔራል ሻምበል ፈረደ
Next articleጠላት ይጥፋ ብሎ ወገን ቢጠራቸው፣ ተነሱ ከእስራኤል ከሞቀ ቤታቸው