
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 41 ዓመታትን የኋሊት ስንጓዝ የእምቢተኝነት ተጋድሎ አሐዱ የተባለባትን ዕለት እናስታውሳለን። ሽብርተኛው ትህነግ የጎመጀበትን የወልቃይት ጠገዴ እና የጠለምት ለም መሬት በጁ አስገብቶ አማራን በባርነት ለማጎሳቆል በተከዜ ወንዝ ክረምት ከበጋ መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ካቦ እና ታንኳ አዘጋጀ። ውጥኑን ሊያሳካ፣ ተፈጥሮ ሳትስት ለወልቃይት አማራዎች የለገሰችውን ሊነሳ፣ ባህል እና ማንነታቸውን ሊያጠፋ፣ በርስታቸው አዝዞ ሊከብር ተከዜን ተሻገረ። በዚህ ጊዜ የወልቃይት ጠገዴ፣ የአርማጭሆ እና የጠለምት ጀግኖች አራስ ነብር ሆነው ጠበቁት፣ እንደ ግስላ ተቆጥተው ከፋኝን በመመስረት ስለ ነጻነታቸው ታግለውታል።
ከፋኝ ትርጓሜው የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ተከዜን ተሻግሮ የበጌ ምድር እና ስሜን ጠቅላይ ግዛትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር ለመዋሰን የሚያስችለውን የትግራይ ካርታ ማስፋፋት፣ ለም መሬት ለማግኘት በርስቱ ላይ የሚኖረውን አማራ የመጨፍጨፍ እና የማጥፋት ፍላጎትን መቃወም ማለት ነው።
ከፋኝን የመሰረቱትም የትግራይን ተፈጥሯዊ ወሰን (ተከዜን) ተሻግሮ ይዞታን ለማስፋፋት የተዘጋጀውን እቅድ የተቃወሙ ጀግኖች ናቸው። እነዚህ ጀግኖች ከጅምሩ በግል እና በቡድን እየሆኑ ሽብርተኛው ትህነግን ተፋልመዋል። ከ1972 ዓ.ም የክረምት ወራት ተጀምሮ የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ ሽብርተኛው ትህነግ ተከዜን ለመሻገር የዘረጋውን ካቦ እንዲበጠስ እና ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀች ታንኳ ከጥቅም ውጪ በማድረግ ትግሉ እንዲቀጣጠል መሠረት የጣሉት ገብሬ ሀጎስ የተባሉ ታጋይ ናቸው።
የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ ሽብርተኛው ትህነግ በረገጣቸው የወልቃይት ጠገዴ፣ የአርማጭሆ እና የጠለምት አካባቢዎች ታላላቅ ሰዎችን፣ ታሪክ አዋቂዎችን፣ ደም አስታራቂ ሽማግሌዎችን እና “ከተከዜ ማዶ የአማራ መሬት ነው” የሚሉ ሰዎችን ለማጥፋት ያገኘውን ሁሉ ሲገድልና ደብዛቸውን ሲያጠፋ ነበር፡፡
ከፋኝ ይህንን በመቃወም በተወሰኑ ሰዎች መስዋእትነት የተጀመረው ፀረ የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ ሽብርተኛው ትህነግ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ አድማሱንም እያሰፋ ቀጠለ። ትግሉ የበለጠ ተፋፍሞ ከወልቃይት፣ ከጠገዴ፣ ከአርማጭሆ እና ከጠለምት የተሰባሰቡ ጀግኖች ነሐሴ 16/1980 ዓ.ም በአብደራፊ ከተማ ተሰባስበው ‘ከፋኝ’ን መሠረቱ፡፡ ከፋኝም የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ ሽብርተኛው ትህነግ መታገልን በተደራጀ አግባብ አጠናክሮ ቀጠለ። በተጠናከረው ትግል የከፋኝ ቡድን ዝና ሲያገኝ እና የተዋጊነት አቅሙ ሲጎለብት የደርግ መንግሥትን ትኩረት መሳብ ጀመረ። በ1982 ዓ.ም የደርግ መንግሥት “ይህ ከፋኝ ያለ ቡድን ማን ነው?” ከፋኝ ማለትስ ምን ማለት ነው?” ሲል ጠየቀ። በከፋኝ እና በደርግ መንግሥት መካከልም ቅራኔ ተፈጠረ።
በዚህም ምክንያት ትግሉ ከተስፋፊው የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ ሽብርተኛው ትህነግ እና ከደርግ መንግሥት ጋር ሆነ። ቅድሚያ አማራን ለባርነት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ያለውን መታገል አስፈላጊ በመሆኑ ከፋኞች ከደርግ መንግሥት ጋር ያላቸውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት ወሰኑ። በወቅቱ የአስተዳደር ስልጣን እንዳላቸው ከሚነገርላቸው ገዛኸኝ ወርቄ ጋር ትክል ድንጋይ ከተማ ተገናኝተው በመወያየት የተፈጠረውን ችግር በእርቀ ሰላም ፈቱ። ቀጥሎም ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኀይለማርያም ጎንደር ከተማ ድረስ ተጉዘው ከከፋኝ ጋር ባደረጉት ፍሬያማ ውይይት የከፋኝ ቡድኑ የትጥቅና የስንቅ ድጋፍ እንዲደረግለት ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበር ማወቅ ተችሏል።
በትዕዛዙ መሠረትም ከፋኞች የጦር መሳሪያ ድጋፍ አግኝተዋል። በዚህም የቀድሞው ትህሃት የአሁኑ ሽብርተኛው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ፣ በአርማጭሆ እና በጠለምት መሬት ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በከፋኝ ቡድኑ ተጋድሎ ተጨናገፈ።
የከፋኝ ቡድኑ ዓላማ “ሽብርተኛው ትህነግ ተከዜን ተሻግሮ አይገዛንም” በሚል የደረሰበትን ኪሳራ እና የከፈለውን መስዋእትነት አይቶ የትግል ስልቱን ቀይሯል። የትግል ሜዳውንም ወደ ወሎ የአማራ ግዛት አዞረ። በተሳሳተ ፖለቲካ ለጊዜውም ቢሆን ሕዝባዊ ድጋፍ አግኝቶ ነበርና በደብረ ታቦር እና በወሎ አቅጣጫ የደርግን መንግሥት እያጠቃ ቤተ መንግሥቱን መቆጣጠር ቻለ። ከፋኝ ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው የጎንደር አካባቢዎች ሀሳቡ ያልተሳካለት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የጠለምትን፣ የወልቃይት ጠገዴን እና የአርማጭሆን መሬት የሚረግጠው በፍርሃት እና በጥርጣሬ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ነበር።
የሀገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላም የመጀመሪያ ተግባሩን በከፋኝ ቡድን ላይ ብቸኛ ዘመቻ አድርጎ ለመመንጠር እንቅስቃሴ አድርጓል። አሸባሪው ትህነግ ስልጣኑን በተቆጣጠረ ጊዜ ከፋኞች ድጋፍ ከማጣታቸው ባለፈ ሊያሳድዳቸው ስለጀመረ አባላቱ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሱዳን እና ኤርትራ መሰደድ ግዴታ ሆነባቸው። ወደ ሱዳን የገቡትን አሸባሪው ትህነግ ከሱዳን መንግሥት ጋር በመመካከር አሳልፋ እንድትሰጥ ስምምነት ላይ ተደረሰ። በዚህም ሱዳን የነበሩት የከፋኝ ቡድን አባላት ወደ ኤርትራ ተሻግረው ትግላቸውን ቀጠሉ። ወደ ኤርትራ ሲሻገሩም የኤርትራ መንግሥት ተቀብሏቸዋል።
በኤርትራ የተሰባሰቡት የከፋኝ ቡድን አባላት ትግላቸውን የበለጠ አጠናክረው ለመቀጠል “የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር”ን መሰረቱ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሽብርተኛው ትህነግ ከትግራይ ተፈጥሯዊ ድንበር ተሻግሮ በያዘው የአማራ ርስት መኖር እንደማይችል ለወገኑ እያስገነዘበ ወያኔን በዱር በገደሉ ተፋለመ፣ የሽምቅ እና የቀጥታ ውጊያ በመግጠም የእንቢተኝነት ትግሉን አጠናክሮ ቆይቷል። አካሄዱ ስጋት የፈጠረበት ወያኔ ስልቱን በመቀየር ድርጅቱን ለመበታተን ከፋኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ምህረት አወጀ። እርሻ መሬትና የከተማ ቦታ እሰጣለሁ በሚል ሽማግሌ አደራጅቶ ላከ። በሌላ በኩል ደግሞ የአርበኞች ግንባር አባላትን ቤተሰቦች ዒላማ ያደረገ ጥቃት ማድረሱን አላቆመም። በዚህም የምህረት አዋጁ ተቀባይነት አላገኘም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በዓላማው ጸንቶ በተጠናከረ ሁኔታ ታገለ። ይህ የከፋኝ ቡድን መመስረትና የትግሉ መቀጣጠል የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ፣ የጠለምት አማራ ማንነት አስመላሽ እና የራያ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በጽኑ አለት ላይ እንዲተከልም መሰረት ሆኗል ይላሉ የትግሉ ባለቤቶች።
ከ20 ሺህ ያላነሰ የወራሪውን እና ሽብርተኛው ትህነግን ቡድን አባላት መደምሰስ እንደቻሉም ይነገራል። በዚህ መካከል አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሕዝብ መራር ትግል ከቤተ መንግሥት ተባረረ። ይህንን ተከትሎም ከኢትዮጵያ የለውጥ መንግሥት ጋር መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። የከፋኝ ቡድኑ መስራችና አባላት አሁንም በፀረ ሽብርተኛው ትህነግ አቋማቸው በመጽናት እስከ አሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ተሰልፈው በመታገል ላይ ይገኛሉ። የከፋኝ ቡድኑ መሥራች አባላት ከተበታተኑበት 1980ዎቹ አማካይ ዓመታት ወዲህ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁመራ ከተማ በአካል ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይቱ የነበረውን የተጋድሎ ሂደት አስታውሰዋል። የወልቃይት ጠገዴ፣ የአርማጭሆ እና የጠለምት ጀግኖች መስዋእትነት ቢከፍሉም ለሽብርተኛው ትህነግ መንኮታኮት እና ከስልጣን መወገድ ከፋኝ የነበረው ሚና ጉልህ እንደሆነ ነው የተናገሩት። የከፋኝ አባላቱ በውይይቱ ላይ እንዳነሱት ትግሉ አሁንም ፍጻሜ አላገኘም። እስካሁን ከነበሩ በደሎች ወደ ፊት ያለው የከፋ ነው እና መላው አማራ ትግሉን ማጠናከር አለበት ነው ያሉት።
በውይይቱ የቀድሞው የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤን እና የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለውን ጨምሮ የክልሉና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ አሸተ የከፋኝ ቡድን አባላቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያደረጉት መራር የነጻነት ትግል ለዛሬ የአሸናፊነት ተምሳሌት እና የነገ ትግል ፋና ወጊ እንደሆነ ተናግረዋል። የገንጣይና አስገንጣይ አስተሳሰብ የወለደውን የባንዳ እንቅስቃሴ ቀድሞ በመገንዘብ፣ በዓላማ ጸንቶ በመታገል፣ መቃወም በማይቻልበት ዘመን በመቃወም እና የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በመፋለም አሸባሪው ትህነግ አንገቱን እንዲደፋ የበኩላቸውን እንደተወጡም አንስተዋል። ዛሬም የጀግና ልጆች በወልቃይት ጠገዴ ታሪክ እየሠሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
“አሸባሪው የትህነግ ቡድን ዳግም ፊቱን ካዞረ ሁሌም እንደምንለው ወልቃይት ጠገዴ መቀበሪያው ትሆናለች” ነው ያሉት።
አቶ ሲሳይ ዳምጤ ቀደምት አባቶቻችን የሠሩት ታሪክ ለዛሬ ትግላችን ስንቅ ሆኖናል ብለዋል። የከፋኝ ሠራዊትም ከጅምሩ ሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድንን በመታገልና ገዝግዞ በመጣል ትልቅ ታሪክ መሥራቱን አንስተዋል። ትግሉ በመላው የአማራ ሕዝብ ብሎም በኢትዮጵያውያን እንዲቀጣጠልና አሸባሪው ዳግም ላይመለስ እንዲቀበር በማድረግ ሂደቱ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m