
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሽብርተኛው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ በከፈተው መጠነ ሰፊ ወረራ የሃይማኖት ተቋማት ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና ውጭ በሆነ መልኩ የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ አሸባሪው እና ተስፋፊው ትህነግ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በከፈተው ወረራ ንጹሃን የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡
ወራሪው ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና ስሪት ባፈነገጠ መልኩ የሃይማኖት ተቋማትን መዝረፉን፣ ማውደሙን እና መዳፈሩን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ወራሪው ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ የፈጸማቸው እኩይ ድርጊቶች ለአማራ ሕዝብ ያለውን ጠላትነት ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

“አሸባሪው የትህነግ ቡድን ዓላማው አሸንፎ ሀገር መምራት ሳይሆን እንደ ሀገር ኢትዮጵያን፤ እንደ ሕዝብ አማራን አንገት ማስደፋት ነው” ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡ የሕዝቡን ሥነ ልቦና ለመጉዳት ሲል የሃይማኖት ተቋማትን ሳይቀር እየተዳፈረ ነው ብለዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ከዋልድባ እስከ ጨጨሆ መድኃኔዓለም የሃይማኖት ተቋማቱ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ መስጂዶች ፈርሰዋል፤ ደረሶችም ቁርአን በሚቀሩበት ቦታ ላይ ተገድለዋል፡፡ ይህ ሁሉ እኩይ ድርጊት የሕዝቡን ሥነ ልቦና ለመጉዳት ሲባል የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የዚህ አሸባሪ ቡድን የጥቃት ሰለባ ለመሆን አማራ ሆኖ መገኘት ብቻ በቂ እንደሆነ ታይቷል፤ በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች ለሕዝብ፣ ለሀገር እና ለሃይማኖት ተቋማት ሲባል ሕዝብን ማስተባበር ይገባል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፡፡
መቀሌ ድረስ በመሄድ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪ አድርገው እንደነበር ርእሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል፡፡ የሽምግልና ባህልን ባልጠበቀ መንገድ አዝነው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ ይህ እየታወቀም በአንዳንድ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶች የቡድኑን እኩይ ድርጊት እና ሀገር የማፍረስ ዓላማውን ባለመገንዘብ አሸማጋይ እና አደራዳሪ መሆናቸውን ሰምተናል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል፡፡

የሕልውና ዘመቻው አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ቧያለው አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ የሰነዘረው ጥቃት እና እየፈጸመ ያለው አስነዋሪ ድርጊት ሁሉ ከታሪክ፣ ከሞራል እና ከእምነት ጋር የሚጣረስ ነው ብለዋል፡፡ የትግራይ ተስፋፊ ኀይል በአማራ ሕዝብ ላይ የቃጣው ጦርነት መጠነ ሰፊ ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና የፕሮፖጋንዳ ጦርነት የተከፈተብን መሆኑን ልብ ማለት ይገባል ነው ያሉት፡፡
“አሸባሪው ትህነግ አማራን ማውደም እንደ ተልዕኮ ይዞ ተነስቷል” ብለዋል አቶ ዮሃንስ፡፡ አሸባሪነት፣ ዝርፊያ እና አማራን እንደ ሕዝብ ማዋረድ የዚህ ጦርነት ባህሪያቶች ናቸው ነው ያሉት፡፡ የሽብርተኘው ትህነግ ቡድን በደረሰበት አካባቢ ሁሉ የቻለውን ተሸክሞ ያልቻለውን ደግሞ አውድሞ ለመሄድ የሚያደርገው ጥረት ዓላማው ማሸነፍ ሳይሆን ማዋረድ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ “በዚህ የሕልውና ዘመቻ የአማራ ሕዝብ ብቸኛ ምርጫ እና አማራጭ ጦርነቱን ማሸነፍ ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና መላው ሕዝብ በጋራ የሚቆሙበት ጊዜ እንደሆነም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ