የመስቀል ደመራ በዓል በኬንያ ናይሮቢ ተከብሯል፤ ኢትዮጵያውያን ተደጋግፈው ለሀገር ልማት እንዲቆሙም ጥሪ ተላልፏል፡፡

205

ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በናይሮቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ደመራ በዓልን አከበሩ፡፡
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በኬንያ የኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልዕክታቸውም የመስቀል በዓል በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሠላም፣ የእርቅና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የጀመረችውን አዲስ የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ለሀገራዊ ሠላም፣ እርቅና አንድነት በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም ነው አምባሳደር መለስ ያሳሰቡት፡፡

‹‹እጅ ለእጅ ተያይዘን በመደጋገፍና በኅብረት ከድህነት ተላቅቃ ዜጎቿ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባትን ታሪከ ገናናዋን ኢትዮጵያን ለመፍጠርም እያንዳንዱ ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ታላቋን ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ ተደጋግፈን መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል አምባሳደር መለስ በመልዕክታቸው።

በናይሮቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት ከዚህ በፊት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛትና የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የኬንያ ‹ቻፕተር›ን በማቋቋም ላበረከቱት አስተዋዕኦ አምባሳደር መለስ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማሳካትም በዕውቀት ሽግግር እና ሀብታቸውን በሀገራዊ ልማት ፈሰስ በማድረግ እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበውላቸል።

የመስቀል በዓል ኢትዮጵያ ለዓለም ስልጣኔ ካበረከተቻቸውና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ ባሕልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው የማይጨበጡ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

ምንጭ፡- በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ

Previous articleየአማራ ክልል ልዑክ ወላይታ ገብቷል፡፡
Next articleየመስቀል ደመራ በዓል በካርቱም መድኃኒዓለም ተከብሯል፡፡