
እኒህ ወራሪዎች የጠፋቸው ቅጡ፣
እንጀራ ልመና ክላሽ ታጥቀው መጡ፣
ቀኑ ወልቃይት ነው ተከዜ ወራቱ፣
መቁጠሪያው ጎንደር ነው ዓመተ ምህረቱ።
ሁመራ፡ ነሐሴ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ደግነት፣ ፍቅር እና ጀግንነት የማይለየው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ተፈጥሮ ምንም ሳትሰስት ያላትን ብትለግሳቸውም አሸባሪው የትህነግ ቡድን ግን ከማጀታቸው ገብቶ ሁሉንም ቀማቸው፣ በርስታቸው ላይ ሰፍሮ በየደረሱበት እየተከተለ ሲያሳድዳቸው ቆየ። በቋንቋቸው እንዳያወሩ አሸማቀቃቸው፣ በአማርኛ ዘፍነው እንዳይጨፍሩ፣ አልቅሰውም እንዳይቀብሩ ባርነት አወጀባቸው። ለዘመናት መሸሸጊያ ጥግ ይፈልጉ የነበሩ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች አሁን ግን እንግዳ ተቀባይ ሆነዋል።
ወልቃይቴዎች የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነት የሚገለጽበት የራሱ የአማራነት ባሕል፣ ቋንቋ፣ ወግ እና የሥነ ልቦና ውቅር አለው። አለባበሱ፣ አመጋገቡ፣ ማኅበራዊ ሥሪቱ፣ ሽለላ እና ቀረርቶው፣ የአጨፋፈር ሥርዓቱ፣ ሐዘን እና ደስታውን የሚገልጽበት መንገድ የጎንደሬነቱ ሕያው ነጸብራቅ ነው። ለብዙ ሺህ ዘመናት ተከዜ በመለስ አማራነት ተከብሮ ሕዝቡም ማንነቱን በነጻነት ሲያንጸባርቅ ኖሯል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአማራ ማንነትን እና የሥነልቦና ውቅር ለማጥፋት የተከተለው ስልት፣ የትግራይ ማንነትን በሕዝቡ ውስጥ በኀይል ለማስረጽ ያደረገው ጫና፣ ሕዝቡ አዲስ ማንነት ላለመቀበል ያደረገውን ተጋድሎ እንዲሁም በመራር ትግል የተገኘውን ነጻነት በአግባቡ ተጠቅሞ በተጽዕኖ ሥር የነበረውን የአማራነት ባሕል፣ ወግ፣ ትውፊት እና ሥርዓት ለማጉላት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የአካባቢው ነዋሪዎች አንስተዋል።
የከፋኝ መሥራችና የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባሉ ልጅእሸት አስፋው እና የነጻነት ትግሉን የተቀላቀለው ተስፋሁን ማንዴ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በጉልበት አካባቢውን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ አማራነትን አጥፍቶ ትግራይነትን ለማስረጽ ያልተከተለው ስልት እንደሌለ ተናግረዋል።
ከማጨት ጀምሮ ጫጉላ ያለውን የሠርግ ሥነ ሥርዓት ብንመለከት እንኳን የሽምግልና ሂደቱ፣ ባሕላዊ የሠርግ ዝግጅቱ፣ ባሕላዊ ትውፊቶቹን ልጅ እያለን እናውቀው ነበር ይላሉ አቶ ልጅእሸት። ነገር ግን ይህ ባሕሉ ለትውልድ እንዳይተላለፍ ብዙ ተሠርቷል ነው ያሉት። አንዲት ልጃገረድን ለመዳር ለአቅመ ሄዋን ስለመድረሷ በሕግ አግባብ እውቅና ሊሰጥ ይገባል በሚል ሰበብ በርካታ ልጃገረዶች በአሸባሪው ትህነግ ካድሬዎች ተደፍረዋል።
በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ድርጊት በመፈጸሙ ብዙዎች ለማኅበራዊ ቀውስና ሥነልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል፣ ትዳራቸውም ተስተጓጉሏል ይላሉ። ይህም አልበቃ ብሎ ለትዳር ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ለመስጠት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይጠየቁ ነበር። ይህን ሂደት አልፎ ሠርግ የሚደግስ ደግሞ ዘፈኑም ሆነ ጭፈራው በትግረኛ እንዲሆን የማድረግ ግዴታ አለበት።
የወልቃይት ሕዝብ ያልነበረኝን ማንነት ተቀብዬ ለልጅ ልጆቼ አላስተላልፍም በማለት ነባር ማንነቱን ለማስከበር ታግሏል። በተለይ ከ1984 እስከ 1987 ዓ.ም ያለቋንቋችን አንዘፍንም፣ ያለባሕላችንም አንጨፍርም በማለት ሙሽሮችን ያለዘፈን እና ጭፈራ ድረዋል ነው ያሉት።
ይህን ለአብነት አነሳን እንጂ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወልቃይት ማንነትን ለማጥፋት አሉኝ የሚላቸውን አማራጮች ሁሉ ተጠቅሟል።
በ1980ዎቹ የራሱን ክራር ደርዳሪ፣ ማሲንቆ ከርካሪ፣ ከበሮ ደላቂ፣ እምቢልታ ነፊ እና ዘፋኝ አደራጅቶ በማሰማራት የወልቃይት አማራዎችን ማንነት በኀይል የማጥፋት ሥራ ጀመረ።
አቶ ተስፋሁን እንዳሉት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነት እና የአኗኗር ዘይቤ የአማራነት ጥግ ማሳያ ነው። የፋሽስት የጡት ልጅ የሆነው ትህነግ የአማራ ሕዝብን የጀግንነት እና የሥነልቦና ጥንካሬ የመንፈስ ትጥቅ የሆነውን ቀረርቶና ፉከራን ጨምሮ ማንነትን ለማጥፋት አዋቂዎችን መርጦ በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት ማጥፋት እንደጀመረ ነው የነገሩን። የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን ጨምሮ የወልቃይትን ነባር ማንነት የሚያንጸባርቁ ቅርሶች ተዘርፈው ደብዛቸው እንዲጠፋም ተደርጓል።
ጫናው ቢበረታም የወልቃይት ሕዝብ የማንነቱ መገለጫዎች እንዳይጠፉና ለባንዳዎች አሳልፎ ላለመስጠት በዱር በገደሉ እድሜ ልኩን ሲዋጋ ኖሯል፣ ታስሯል፣ ተገድሏል፣ ብዙ ግፍና መከራን ተቀብሏል።
በሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ መሠረት እንዲመለስ ጥረት ቢደረግም ችግሩ እየተባባሰ እየከፋ ሄዷል። ምን ጊዜም ሐቅ የሌለው ትግል መጨረሻው ፈራሽ ነውና ከብዙ መስዋእትነት በኋላ የወልቃይት ሕዝብ ነጻነቱን አውጇል ብለዋል።
አቶ ተስፋሁን ወልቃይት ነጻ ከወጣች በኋላ በታደሙባቸው ሠርጎች ነባሩ ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ እንደተጀመረ ተናግረዋል። የወልቃይት ሕዝብ ጀግንነቱን፣ አብሮነቱን፣ መተዛዘኑን፣ መከባበሩን፣ ደስታውን እና ስሜቱን የሚያንጸባርቅበትን አንኳር የማንነት መገለጫ ጠብቆ ለማቆየት በ2008 ዓ.ም የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የባሕል ቡድን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ጀምሯል። እንቅስቃሴው መስዋእትነት ቢያስከፍልም ትግሉ አንጸባራቂ ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል።
በጉልበት የተወሰደው ማንነት በእልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋእትነት ከተመለሰ በኋላ በተጽዕኖ ስር ሆኖ የደበዘዘውን ባሕል ማጉላት፣ የጠፋውን ፈልጎ በተገቢው መንገድ ማስተጋባት እና የተገኘውን የነጻነት አየር በአግባቡ መጠቀም ቀጣዩ የቤት ሥራ እንደሆነ ነው የሚገልጹት። ለዚህም አሸባሪው ትህነግ ለዘመናት ባደረሰባቸው ፖለቲካዊ ግፍና በደል ምክንያት አካባቢውን ጥለው ወደተለያዩ ሀገራት የተሰደዱ አማራዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ እና ተገቢውን ፖለቲካዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠይቃል።
ትህነግ የሚባል ቡድን ነበር በሚባልበት ደረጃ ማጥፋት ካልተቻለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ጊዜም ረፍት ስለማይኖረው አሸባሪውን ቡድን ባጠረ ጊዜ ለማጥፋት የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል። አሸባሪው ቡድን የወልቃይት ጠገዴን ምድር እንዳይረግጥ ጠንክሮ ከመከላከል ባለፈ ወግና ባሕልን ለማሳደግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አቶ ተስፋሁን አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ-ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m