
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ በአራት ግንባሮች ውጊያ የከፈተው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን እየተቀጠቀጠ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ያለዓለም ፈንታሁን ገልጸዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው እንደተናገሩት ወራሪውና አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ንጹሐንን እየገደለ፣ እያፈናቀለ፣ ሃብትና ንብረት እየዘረፈና እያወደመ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን የሽብር ቡድን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና ሕዝቡ በቅንጅት እየደመሰሱት ነው፤ በሰሜን ጎንደር ዞን የገባው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በወገን ጦር እየተደመሰሰ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ያለዓለም አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በዞኑ በአራት ግንባሮች ውጊያ ከፍቶ እየተመታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጅሬ ጃኖራ የገባውን የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ሚሊሻውና ፋኖው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እየደመሰሰው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዳባትና በደባርቅ መካከል ጭና በተባለ አካባቢ ቆርጦ ለመግባት ጥረት ያደረገው አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን አብዛኛው ተመትቷል፤ የቀረው ወደታች አፈግፍጓል፤ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻውና ፋኖው እየተከታተለ እየቀጠቀጠው ነው ብለዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት ትናንት በጭና በተደረገው እልህ አስጨራሽ ውጊያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ተደምስሷል፤ ከሞት የተረፈው ኀይል ወደታች አፈግፍጎ ወርዷል፤ በሸጡ ተቆርጦ የቀረውን ቡድን በመከታተል እየተደመሰሰ ነው ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ውጊያ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አስደናቂ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጎን በመሆን ታላቅ ሥራ እየሠራ ነውም ብለዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ በሚያስደንቅ ተሳትፎ ወደ ውጊያ መግባቱን ነው አቶ ያለዓለም የተናገሩት፡፡ “ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርገነዋል” ነው ያሉት፡፡
አቶ ያለዓለም የደባርቅ፣ የዳባትና የወቅን ወጣቶች ከተማቸውን ከሰርጎ ገቦች ከመጠበቅ ባለፈ ወደ ጦርነት መግባታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
አቶ ያለዓለም አሸባሪው ቡድን አማራን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ማፈራረስ ዓላማው አድርጎ መነሳቱን ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ ለትግል መውጣቱን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ሕዝባዊ ጦርነት እየተካሄደ እንደሆነም ነው የጠቀሱት፡፡
ጠላት በገፍ የሚያመጣውን ኀይል ለመመከትና ለመደምሰስ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና አጠቃላይ ሕዝቡ በተጠናከረ ሁኔታ ወጥቷል ብለዋል፡፡ የሚመጣው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ባለበት እያለቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድንን በገባበት ለማጥፋት እየተደረገ ባለው ዘመቻ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ርብርብ እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አሁን ካለው ትግል ባለፈ ወጣቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን እና ልዩ ኀይልን በመቀላቀል ሀገርን ማገልገል ግድ እንደሚለው ነው አቶ ያለዓለም ያነሱት፡፡ ከችግር መውጫ መንገዱ እንደ ሕዝብ አንድ ሆኖ መቆም ሲቻልና መከላከያ ሠራዊቱንና ልዩ ኀይሉን ማጠናከር ሲቻል ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ አሁን በጀመረው መንገድ ሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን ሕዝብ ሊያዋርድ እንደመጣ ተገንዝቦ እንዲፋለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m