
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአረብኛ ቋንቋ ዘገባዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም አለኸኝ አስታወቁ።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአረብኛ ቋንቋን ሥራ ማስጀመር አስመልክተው የቦርድ ሰብሳቢው አብርሃም አለኸኝ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ዘገባ ተደራሽ እያደረገባቸው ከሚገኙ ቋንቋዎች በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን ለመጠቀም ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ የውጭ ቋንቋዎችን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ቅድመ ዝግጅት ሲያደረግ መቆየቱን አስታውቀዋል።
አቶ አብረሃም በአረብኛ ቋንቋ ሥርጭት ማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል። ሚዲያው በአረብኛ ቋንቋ ከሰኞ እስከ አርብ ሥርጭት እንደሚኖረው ነው የተናገሩት። የአረብኛ ቋንቋ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በቋሚነት አገልግሎት ላይ ይውላል ነው ያሉት። ሚዲያው የቋንቋ ተደራሽነቱን ለማስፋት ሁለተኛ ቻናል “አሚኮ ኅብር” መጀመሩን ያነሱት ቦርድ ሰብሳቢው በሁለቱም ቻናሎች የተለያዩ ዝግጅቶችን እያስተላለፈ መሆኑን ገልጸዋል።
የቋንቋ ብዝኃነትን አክብሮና ፋይዳውን በመገንዘብ ቋንቋውን ከሚናገረው ማኅበረሰብ ጋር የዕለት ከዕለት ግንኙነት ማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
አረብኛ ቋንቋ በሀገር ውስጥ ጨምሮ በቀጣናው በርካታ ተናጋሪዎች ያሉት ቋንቋ መሆኑን ያነሱት አቶ አብርሃም በመካከለኛው ምሥራቅና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ቋንቋ ነው ብለዋል፡፡ የአረብኛ ቋንቋን መጠቀም ለአማራ ክልል ሕዝብ መስተጋብር፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እሴቶችን አስተሳስሮና አልምቶ ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የአማራን ሕዝብ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር በማግባባት ወንድማማችነትን ለመገንባት ያስችላልም ብለዋል። ኢትዮጵያን ለማወቅ ጉጉት ያላቸው ሕዝቦች ቋንቋቸውን ስንጠቀም እኛን እንዲያውቁ የማድረግ እድል አለውም ነው ያሉት።
አቶ አብርሃም “ቋንቋ መስታወት ነው፤ እርስ በርስ እንድንግባባ፣ እንድንተያይ የሚያስችል ትልቅ መሳሪያ ነው፤ የአረብኛ ቋንቋን መጠቀማችን ከአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ጋር ያለንን ግንኙነት እያጠናከርነው እንድንሄድ ያስችላል” ብለዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለሁሉም ቋንቋዎች እኩል ዋጋ ይሰጣል ያሉት አቶ አብርሃም ሁሉንም ቋንቋዎች ወደ ሥርጭት የማምጣት ፍላጎት እንዳለም ነው ያነሱት። አቅም በፈቀደ መጠን ከራሳችን ሁኔታ ጋር እያገናዘብን በርካታ ቋንቋዎችን የምንጠቀምበት ምቹ ሁኔታ ይኖራል ነው ያሉት። ሚዲያው የግእዝ ቋንቋን ለመጠቀም ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከመነሻው ጀምሮ ተወዳዳሪ ሚዲያ ለመሆን እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ አብርሃም ተወዳደሪ እንዲሆን ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መታጠቅ አለበት፤ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል የሰው ኃይል ሊኖር ይገባል፤ ሁሉንም ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አቅምን ማዕከል ያደረገ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራትና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል። ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መጠቀም ካልቻልን መሪዎች ሳንሆን ተከታዮች ነው የምንሆነው፤ ራሳችንን ለዓለም ተደራሽ የሚያደርግ የሚዲያ ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን ነው ያሉት። በቀጣይ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ከፍ ያለ አቅም ያለው ተቋም እንዲኖር እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m