
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ ተቋማት ዓይንና ጀሯቸውን ቢነፍጉትም ማይካድራ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ የዘር ማጥፋት ወንጀል በአደባባይ የተፈጸመበት ቦታ ነው። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ብቻ በፈጸመው ዘር ተኮር ጅምላ ጭፍጨፋ 1 ሺህ 563 ሰዎች በጅምላ መገደላቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት አረጋግጧል።
እስካሁን ድረስም ተጨማሪ አስከሬን እየተገኘ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በጅምላ መቃብር ስፍራው የሰማእታት መታሰቢያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል። የመርኃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማ መስዋእት የሆኑ ንጹኃን ወገኖችን በቋሚነት መዘከር ነው። ችግኙን ያዘጋጀው የመተማ ወረዳ ሲሆን የምዕራብ ጎንደር እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞንኖች መርኃግብሩን በጋራ አካሂደዋል
ይህም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በግፍ የጨፈጨፋቸውን አማራዎች በቋሚነት ከመዘከር ባለፈ መስዋእትነት የከፈሉለትን ዓላማ ከዳር የማድረስ ተልዕኮ እንዳለው የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ በሕልውና ትግሉ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ባለበት ጊዜ መርኃ ግብሩ መከናወኑን በማንሳትም እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በሕብረት መመከትና ሕዝቡን ከጉዳት መታደግ እንደሚገባ ማሳያ እንደሆነ ነው ያስታወቁት። የማይካድራ ንጹኃንን በግፍ የጨፈጨፈውን አሸባሪ ቡድን ለመቅበር በሕብረት እንደሚሠሩ ነው ያስታወቁት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪው ሀብታሙ አለልኝ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አሳፋሪ ሽንፈትን በተከናነበ ጊዜ ንጹኃንን በጅምላ በመጨፍጨፍ እየሞተ እንኳን ለአማራ ሕዝብ ያለውን የጥላቻ ጥግ ያሳየበት ነው ብለዋል።
ለዚህ መጥፎ ታሪክ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሁለቱ ዞኖች ዛሬ የመጀመሪያ ዙር የችግኝ ተከላ አካሂደዋል። ቀጣይም “አሸባሪውን ወራሪ ቡድን እያጠፋን አካባቢያችንን እናለማለን” ነው ያሉት።
በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ የሁለቱ ዞኖች ተወካዮች፣ የሕልውና ዘመቻው አስተባባሪዎችና በማይካድራ ጭፍጨፋ የተሰው ሰማእታት ቤተሰቦች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m