የአማራ ክልል ልዑክ ወላይታ ገብቷል፡፡

427

ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአማራ ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በዮዮ ግፋታ (የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል) ለመሳተፍ ወላይታ ገብቷል።

ልዑኩ በወላይታ ቆይታው የሁለቱን ሕዝቦች ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ታውቋል።

የወላይታ ሕዝብ የሀገር ሽማግሌዎች በአዲስ ዓመት መግቢያ ላይ በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር በመገኘት ለክልሉ ሕዝብ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው ነበር። የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል (ዮዮ ግፋታ) ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።

የክልሉ መንግሥትም ጥሪውን ተቀብሎ የሥራ ኃላፊዎችን ወደ ወላይታ ልኳል። የልዑኩ ጉዞ የአማራ እና የወላይታ ሕዝቦችን ታሪካዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው፣ የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ልጃለም እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የክልል የሥራ ኃላፊዎች ናቸው ወደ ወላይታ ያመሩት።

በሥፍራው ሲደርሱም በወላይታ ወጣቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ነገ በወላይታ ስታዲዬም ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ መርሀ ግብሩ ያሳያል።

ምንጭ፦ የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት

Previous articleየመስቀል በዓል እና የአረጋውያን ትዝብት፡፡
Next articleየመስቀል ደመራ በዓል በኬንያ ናይሮቢ ተከብሯል፤ ኢትዮጵያውያን ተደጋግፈው ለሀገር ልማት እንዲቆሙም ጥሪ ተላልፏል፡፡