“የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኡጋንዳና ሩዋንዳ ጉብኝት ውጤታማ ነበር” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

261

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኡጋንዳና ሩዋንዳ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከሀገራቱ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር ረገድ ውጤታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገሮች ያደረጉት የሥራ ጉብኝት ውጤማ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቆይታቸውም ከሀገራቱ መሪዎች ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መመክራቸውን ተናግረዋል።

ሀገራቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት በጋራ መፍታት እንዳለባቸው መወያየታቸውን ጠቁመው፤ ጉብኝቱ “ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክሮታል” ብለዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያን አቋም ማንጸባረቁን አስታውሰዋል።

በተለይም አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል አመልክተው፤ በሀገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ላይም ጣልቃ መግባት እንደማያስፈልግ በግልጽ መናገራቸውን አውስተዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የዚህ ሁሉ ችግር አሸባሪው የህወሓት ቡድን መሆኑን ሀገራቱ እውቅና መስጠታቸውን ገልጸው፤ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔም በአዎንታ ተመልክተውታል ነው ያሉት።

እነዚህም ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን መንግሥት በአድናቆት እንደሚመለከተው ገልጸው፤ አሁንም አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ሆኖም አሁንም በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ያልተረዱ በተቃራኒው የተሰለፉ ሀገራት መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህንም አገራት ለማስረዳት “ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ይጠናከራሉ” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው፤ ለዚህም በመንግሥት የተካሄዱ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ጎን ለጎንም በኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚካሄደው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን እየያዘ ለመጣው አዎንታዊ አቋም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

ዜጎች በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙኀን በመቅረብ የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም ያስተዋወቁበትም ጥረት ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም ሚኒስቴሩ አሁን ላይ መደበኛውን የዲፕሎማሲ ሥራ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጋር በማጣመር ለተሻለ ውጤት መትጋት በሚያስችለው ቁመና ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን ከቱርክ አምባሳደር ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ።
Next article“ከወለድኩ ሁለት ቀኔ ነው፤ አሸባሪው ትህነግ በቀያችን ጥቃት በመክፈቱ ለመሰደድ ተገድጃለሁ” ከሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የተፈናቀሉት ወይዘሮ ዘምዘም አሊ