
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሕዝብ በሕልውናው ዘመቻው ለተሰለፉ የወገን ኃይሎችና በአሸባሪው ትህነግ ለተጎዱ ዜጎች ከ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እህልና የቁም እንስሳት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ የተለያዩ ዞኖች በህልውና ዘመቻው የጸጥታ አካላትን በግንባር በማዝመት አሸባሪውን ቡድን እየደመሰሱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
የተደረገው ድጋፍ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ያጠናክረዋል ብለዋል።
አቶ ቀለመወርቅ ጠላት እንዲሸነፍ ያደረገው የሕዝብ አንድነት በመኖሩ እንደሆነም ነው ያስረዱት። ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የነፋስ መውጫ ከተማ እና አካባቢው ማኅበረሰብም ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት ብርጋዴየር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ጠላትን በተባበረ ክንድ እየተደመሰሰ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ባለው አቅም ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ለሠራዊቱ ያለውን አጋርነት እያሳየ እንደሆነም ነው የተናገሩት። የሕዝቡ ድጋፍ ለሠራዊቱ ከፍተኛ ሞራል መሆኑንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ስሜነህ አያሌው ሕዝቡ በተባበረ ክንድ አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን መደምሰስ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
የተደረገው ድጋፍ በግንባር ለተሰለፉ የወገን ኃይሎችና በአሸባሪውና ወራሪው ቡድን ለተጎዱ ወገኖች የሚውል መሆኑን አስረድተዋል።
የሚደረገው ድጋፍ ቀጣይነት ያለው መሆኑንም አቶ ስሜነህ ገልጸዋል። ድጋፉ 182 ሰንጋዎች እና 711 ኩንታል እህል እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከነፋስ መውጫ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m