
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል ቅዠት ከተደበቀበት ዋሻ በመውጣት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በንፁሃን ዜጎችና በንብረት ላይ ውድመት እየፈፀመ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ በመነሳት የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን የህወሓት የሽብር ቡድን እስከ መጨረሻው ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በጋራ ተነስተዋል።
ብርጋዴር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አንደኛ ኮር አዛዥ ይህ ወራሪ ኀይል ሰርጎ በገባባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ሽንፈትና ኪሳራ ደርሶበታል። ለዚህ ድል መገኘት ደግሞ የሜካናይዝዱና የእግረኛ ተዋጊዎች ጥምረት ጉልህ ነው ብለዋል።
ኮሎኔል ዘለቀ አለባቸው የጨጨሆ ግንባር የሜካናይዝድ ክፍሎች አስተባባሪ እንዲሁም የአየር ኀይል እና የምድር ኀይል አስተባባሪ እንደገለፁት የእግረኛ ተዋጊዎች እና የሜካናይዝድ ክፍሉ በከፍተኛ የውጊያ ጥበብ በመመራቱ ወራሪው ኀይል ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት የዘረፈውን ንብረት ጥሎ እየፈረጠጠ ነው፤ እኛም እየተከተልን እየደመሰስነው እንገኛለን። ሕዝብም በየአካባቢው እየሸሸ የሚመጣውን ጠላት በመፋለም ታሪክ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ኮሎኔል ወርቁ አሸናፊ የ5ኛ ሜካናይዝድ ኦፕሬሽናል ምክትል አዛዥ በበኩላቸው ይህን የሽብር ቡድን የምንዋጋው ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ለመጠበቅ ነው። እኩይ ዓላማን ተሸክሞ የሚንቀሳቀሰውን ጠላት በአጭር ጊዜ ለመቅበር ደግሞ በቅንጅት እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
የእያንዳንዱ ድል ባለቤት የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችን ሆኖ እያደረገ ላለው ድጋፍ እናመሰግናለን። ይሄን አውዳሚ ቡድን በአጭር ጊዜ በማጥፋት ለሕዝባችን የድል ዜና እናበስራለን ሲሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ መግለፃቸውን የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m