ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሚዛናዊ እይታ እንዲኖራቸው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጠየቁ፡፡

200

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ አዴል ክኾድር ከአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባሕር ዳር ውይይት አድርገዋል፡፡

ከውይይታቸው በፊት ትናንት በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን እንደጎበኙ የገለጹት የዩኒሴፍ ተወካይዋ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው እና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ወረራ ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፋቸውን፤ በርካቶችም ለቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን ርእሰ መስተዳድሩ ለአዴል ክኾድር ገልጸውላቸዋል፡፡ ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ በገለፃቸው አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ውድመት፣ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ዘረፋ ፈጽሟል ብለዋል፡፡

በዚህም በክልሉ መጠነ ሰፊ ጉዳት ደርሷል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

የአሸባሪው ቡድን ወረራ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት በአማራ ሕዝብ ላይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲሰነዘር የነበረው ትችት መሰረተ ቢስ እንደነበር አመላካች ነው ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡

ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሚዛናዊ ዕይታ እንዲኖራቸውም ጠይቀዋል፡፡ በጦርነት ወቅት ድምፃቸው ለማይሰማ ግፉዓን ጥብቅና መቆም እና ድምጽ መሆን ተገቢ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መርጦ አልቃሽነት ግን ይህ የፈተና ወቅት ሲያልፍ ተቋማቱን ትዝብት ላይ የሚጥል እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ዩኒሴፍ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ችግር ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ዩኒሴፍ ለአማራ ክልል ለችግር ጊዜ ደራሽ በመሆኑ አመሥግነዋል።

ድጋፉ ለተማሪዎች ደብተር እና እስኪርቢቶ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሁም ፍራሾች እና ሌሎች ቁሳቁስ ያካተተ ነው ፡፡

በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ አዴል ክኾድር በጦርነቱ በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ ጉዳቶች መድረሳቸውን እንዳስተዋሉ ተናግረዋል፡፡

ድርጅታቸው አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ለመድረስ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ዩኒሴፍ በመላው ዓለም ለሚገኙ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሕጻናት ጥብቅና ይቆማል ያሉት ተወካይዋ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ጉዳዩን ሊያጤኑት እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን የክፋት ጥጉን በሕጻናት ላይ ፈጽሞ አሳይቷል።
Next articleበማይጠብሪ ግንባር በደባርቅ ወረዳ በጫንቅና በዳባት ወረዳ ጭና ቆርጦ ለመግባት የሞከረው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተደመሰሰ።