
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን ሰላምን ገፍቶ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ወርሮ በንጹሃን ላይ ግፍ እየፈጸመ ነው። ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን በግፍ በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ንጹኃንን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፣ ንብረት ዘርፏል፣ አካል አጉሏል፣ ሕይወትን ቀጥፏል፡፡ ዘርፎ መውሰድ ያቃተውን ንብረት በማቃጠልና በማውደም የክፋት ጥጉን ለዓለም አሳይቷል፡፡
ሕጻን ዮናስ ካሳው ይባላል፡፡ ወደዚች ምድር ከመጣ ገና ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ የእናቱን ጡት ጠብቶ አልጨረሰም፣ ጠንክረው መቆም ባልቻሉ እግሮቹ ድክ ድክ እያለ የአባቱን እግር ይከተላል፤ አባትም የልጁን የነገ ተስፋ ለማየት የምንግዜም ምኞቱ ነው።
አርሶ አደር ካሳው ጥጋቤ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በፋርጣ ወረዳ የጋሳይ ቀበሌ ነዋሪ ነው፤ ሮውንም በስጦታ ባገኛት ሩብ ሄክታር መሬት እና በቀን ሥራ ቤተሰቡን ያስተዳድራል። የሁለት ልጆች አባት የሆነው አርሶ አደር ካሳው የመጀመሪያ ልጁ የ12 ዓመት ስትሆን ሁለተኛ ልጁ ደግሞ የ3 ዓመት ሕጻን ነው፡፡ አርሶ አደር ካሳው የትህነግ ወራሪ ቡድንን ለመመከት ወደ ወረዳቸው የመጣውን መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በልዩ ልዩ መልኩ ደግፏል፡፡
ሽብርተኛው ቡድን ወደ ከተማዋ ከገባ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት የተረዳው አባት የ12 ዓመት ልጁን ወደ ገጠር አሽሽቶ ሕጻን ልጁ እና እናቱ ከእሱጋር እንዲቆዩ አደረገ፡፡ ሽብርተኛው ቡድን ጋሳይን እና አካባቢውን በመቆጣጠሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ቤት ዘረፈ፣ ንብረት አወደመ፣ ሴቶችን እና አረጋውያንን ለእንግልት ዳረገ፡፡
በዚህ ወቅት አርሶ አደር ካሳው እና ቤተሠቡ ቀን በጫካ እየዋሉ ሌሊት የረሀብ ጠኔያቸውን ለማስታገስ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ አሸባሪው ቡድን ለአራት ቀናት ጋሳይን ይውረራት እንጅ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ መግቢያ እና መውጫ ሲያሳጣው አካባቢውን ለመልቀቅ ቢገደድም ለጥፋት የሰነዘረው እጁ የአርሶ አደር ካሳው ሁለተኛ ልጅ ላይ የማይሽር ጠባሳ አስቀመጠ፡፡
አሸባሪው ቡድን የላከው ከባድ መሳሪያም ሕጻን ዮናስ ካሳው አንድ እግሩን እንዲያጣ ምክንያት ሆነ፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጋሳይ ላይ ስቃይ ማብዛቱ ወጣቶች የክፋት ጥጉን አውቀው እንዳይገባ ጥረት ማድረጋቸውን ከውስጥ ባንዳዎች በማረጋገጡ ነው ይላሉ፡፡
አርሶ አደር ካሳው በእጁ ይዞ ከሚያስታምመው ጉዳተኛ ልጁ በተጨማሪ የወንድሟን ጉዳት ያልሠማችው የ12 ዓመት ልጁ መሠረት ካሳው ጉዳቱን አምና ለመቀበል እንደምትቸገር ሀዘን ባቆሰለው ልቡ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ ካሳው በጋሳይ ጉዳት የደረሰበት ልጁን በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል እያሳከመ ይገኛል፡፡
የሕጻን ዮናስ ጉዳት የልጇን ነገ አስቀድማ ለምታልም እናት ሸክሙ ከባድ ሆኗል፡፡ እናት ወይዘሮ ዳሳሽ ጥጋቤ የልጇን ጉዳት ከንግግር ይልቅ በእንባዋ ጅረት ገለጸችው፡፡ ከመናገር ይልቅ ፊቷ በእንባ እየታጠበ ንግግሯን ሳግ ገታው፡፡ የልቧ ጠባሳ ይሽር ዘንድ አሸባሪው የትግራይ ቡድን ተደምስሶ ሀገሯ ንጹሕ አየር የምትተነፍስበት እንድትሆን መመኘቷን ግን በሲቃዋ መካከል ገልጻለች፡፡
አርሶ አደር ካሳው በልጁ የደረሠው ጉዳት ልቡን ቢሠብረውም ወራሪው እና አሸባሪው የትህነግ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት፣ በልዩ ኀይል፣ በሚሊሻ እና በፋኖ ተቀጥቅጦ አካባቢውን መልቀቁና ቢያስደስተውም የጥፋት ቡድኑ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በአጭር ጊዜ መደምሰስ እንዳለበትም ነግሮናል፡፡
አቶ ካሳው አሸባሪው የትህነግ ቡድን የአማራ ክልል አካባቢን ለቆ እንዲወጣ በሚደገረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለሌሎች የሚራራ ልብ የለውም እና በሁሉም አካባቢ ጉዳት እንዳያደርስ ወጣቶች ተግተው አካባቢያቸውን መጠበቅ፣ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ድጋፍ ማድረግ፣ ሥንቅ እና ትጥቅ ማቀበል ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአርሶ አደሮች ጸብ የለኝም ይበል እንጅ በትውልድ ላይ የዘመተ ጠላት ለመሆኑ ማሳያው የኔ ልጅ ነው ብሎናል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m