
ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) የመስቀል በዓል በባሕር ዳር ሲከበር በበዓሉ ላይ ያሉትን አዳዲስ ነገሮች ባየሁበት ልክ ለተከታታዮቻችን ለማድረስ አስፈላጊ የምስል እና ድምጽ ማስቀሪያ መሳሪያዎቼን ይዠ ወደ መስቀል አደባበይ ሄጀ ነበር፡፡ መስቀል አደባባይ ለመድረስ ዙሪያ ገባየን እየቃኘው ጉዞየን ቀጥያለው፡፡
በጉዞየም ግራና ቀኝ ሁለት ዓይነት የበዓል ሁለቶች ይታዩኛል፡፡ በሰፈራቸው ደመራ ደምረው በዓሉን ለማክበር ተፍ ተፍ የሚሉ የአንድ አካባቢ ሰዎች በየሰፈራቸው ሥራቸውን ይከውናሉ፡፡ በሌላ በኩል በዓሉን በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ለማክበር በአንድ እጃቸው ችቦ በሌላ እጃቸው ደግሞ ቄጤማ ይዘው የሚጓዙ አሉ፡፡ እኔም ጉዟውን ወደ መስቀል አደባባይ ወዳደረጉት አዛውንቶች ተጠግቼ የእንኳን አደረሳችሁ ምኞቴን ከገለጽኩና እነሱም አጸፋውን ከመለሱልኝ በኋላ ስለመስቀል በዓል ያላቸውን ትዝታ እንዲያጫውቱኝ ጠየኩ፡፡ ደስ ብሏቸው ተራ በተራ ትዝታቸውን አጫውተውኛል፡፡ በቆይታችን ፊታቸው ላይ ደስታና የበዓል ድባብ ይታይ ነበር፡፡
አቶ በዛብህ ተገኘ ተወልደው ያደጉት ባሕር ዳር ከተማ እንደሆነ ነግረውኝ “ድሮ እኛ ወጣት እያለን፣ በዓሉን ስናከብር እንደዚህ ብዛት አልነበረንም” ሲሉ ጭውውታችንን ጀምረውታል፡፡ እንደ አዛውንቱ ገለጻ ቀደም ባለው ጊዜ በየአካባቢው የመስቀል በዓል ሲከበር የሰዎች ቁጥር እንደ አሁኑ ዘመን ብዛት አልነበረውም፡፡ “ቢሆንም ጎረቤታሞች ተሰባስበን፣ አንዳችን ከአንዳችን ቤት በመሄድ አብረን እየበላንና እየጠጣን፣ በፌሽታ እየጨፈርን እናከብረው ነበር” ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የሕዝብ ቁጥር ጨምሮ መተሳሰቡ የቀነሰ እንደመሰላቸው አጫውተውኛል፡፡ “በወጣትነት ዘመናችን ከቤታችን መጥቶ የሚበላ ሰው እምብዛም አናገኝም ነበር፣ ብናገኝ ግን ደስታችን ወደር የለውም ነበር፤ የአሁኑ ትውልድ ግን በዚያ ልክ ሲተዛዘን አናስተውልም” ነው ያሉት፡፡ ‹‹ሃይማኖትን ማክበር እና መውደድ አቅመ ደካማን መደገፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጊዜው ተለዋውጦ ዘመናዊነት ቢያይልም መከባበር ያስፈልጋል›› ነው ያሉት አዛውንቱ ድሮን ከዘንድሮ እያነጻጸሩ ሲያጫውቱኝ፡፡
ወይዘሮ የሺ ፀጋዬም በጉዞየ ያገኘኋቸው እናት ናቸው “ድሮ በገጠር ተሰባስበን ቆሎ ቆልተን፣ አበባየውሽ ብለን ነበር መስቀልን የምናከብረው” በማለት የኋሊት በምናብ ተጉዘው የገጠር በዓል አከባበራቸውን አስታውሰውናል፡፡ ወይዘሮ የሺ አሁን አሁን ባሕሉ እየተቀየረ መምጣቱን ነግረውናል፡፡ ወጣቱ ለሃይማኖቱ እጅግ ተቆርቋሪ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ የሺ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያውያንን የማይገልጽ አለባበስ መመልከታቸውን ግን ነግረውናል፡፡
“ድሮ ሕዝብ እንደዚህ ወጥቶ በዓል ሲያከብር አይቼ አላውቅም፤ ይህ ብቻ ሳይሆን በመስቀል በዓል ላይ ፈረንጅም ዓይተን አናውቅም” ያሉን ደግሞ አቶ አይችሌ ተፈራ ናቸው፡፡ ‹‹በደመራ በዓል ጥቂት ሰዎች ብቻ ይወጡ ነበር፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ነው የሚያብረው፡፡ በዚህም አገራችን በመስቀል በዓል ምክንያት የቱሪስት መዳረሻ መሆን ጀምራለች፤ ይህም አስደስቶኛል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ብሩክ ተሾመ