“አሸባሪው ትህነግ በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ለመግባት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

644
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል ላይ በከፈተው ወረራ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን ፈጽሟል፡፡ ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች ንጹሃንን ገድሏል፣ አስነዋሪ ድርጊቶችን ፈጽሟል፣ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፣ የመንግሥት ተቋማትን እና የግል ድርጅቶችን ዘረፏል፡፡
ቡድኑ በየአካባቢው በፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ምክንያት በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ጉዳት ተጋልጠዋል፡፡ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስም የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ጥሪ አስተላልፎ የሕልውና ትግል ውስጥ ተገብቷል፡፡
በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ለሕልውና ዘመቻው ከሚያደርጉት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮችን እና አደረጃጀቶችን በመፍጠር አካባቢያቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ 593 ቀበሌዎች የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮችን እና አደረጃጀቶችን በመፍጠር ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ ሙሃመድ ገልጸዋል፡፡
“ተስፋፊው አሸባሪ ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ሰብሮ ለመግባት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም” ያሉት አቶ ሰይድ በተለይም በተሁለደሬ ሚሌ፣ ወረብ አቦ፣ ውጫሌ እና ደላንታ አካባቢዎች ሰብሮ ለመግባት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል ብለዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ የአማራ ሕዝባዊ ሰራዊት፣ ፋኖ እና ወጣቶች በአደረጉት ጠንካራ እና የተደራጀ መከላከል አሸባሪው ቡድን በተደጋጋሚ ተመትቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህ ጠንካራ አደረጃጀት ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዞኑ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪም በአጎራባች አካባቢዎች እና ሌሎች ዞኖች በሚደረገው የሕልውና ዘመቻ ላይ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከአማራ ልዩ ኀይል ጎን ተሰልፈው የሚፋለሙ ሚሊሻዎችን አሰማርቷል ነው ያሉት፡፡
አቶ ሰይድ ጠላት በገባባቸው አካባቢዎች የፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት በሚገባ ሕዝቡ እንደተገነዘበ ገልጸው አካባቢን ለቆ ከመፈናቀል እና ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ከመፈጸሙ በፊት ፊት ለፊት ተዋግቶ አካባቢውን፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን ማዳን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ሀገራችን የገጠማትን የህልውና ፈተናና የህዳሴ ግድባችንን በድል አጠናቀን የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን❞ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን
Next article”ከአጼ ሚኒልክ ታሪክ የምትጋራው ውጫሌ እንግዳን አሜን ብላ መቀበል እንጅ ባንዳንና ከሀዲን የመቀበል ታሪክ የላትም“ የአንባሰል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ጌታቸው ጽጌ