
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ በርሚንግሃም እና ኮቨንተሪ ከተሞች ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ የማሳበሰቢያ መርኃግብር ተካሂዷል።
ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረገውን የህልውና ዘመቻ እንደሚደግፉ በበርሚንግሃም እና ኮቨንተሪ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ገልጸዋል።
ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጠሉም ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ የማንነታችን መገለጫ ነው ያሉት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ❝ሀገራችን ያቀረበችልንን ጥሪ ምላሽ መስጠት የዜግነት ግዴታችን በመሆኑ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ተካሂዷል❞ ነው ያሉት፡፡
ሀገራችን የገጠማትን የህልውና ፈተናና የህዳሴ ግድባችንን በድል አጠናቀን የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን ብለዋል ኢትዮጵያውያኑ፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ያለው ለውጥ በሕዝብ ትግል የመጣ በመሆኑ አንድነታችንን እና ሕብረታችንን ይበልጥ በማጠናከር ልንጠብቀውና ልንደግፈው ይገባል ነው ያሉት፡፡
እርስ በርስ እንዳንግባባ ያደረገን ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዷል ያሉት አምባሳደር ተፈሪ “ግድቡ የእኔ ነው” በሚል መርህ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግና የሀገር ህልውናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ዘመቻ በአንድነት መቆማችሁ ለዚህ ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ በመላው ሕዝብ ትብብር በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደረገ ሰፊ ርብርብ ወደመጠናቀቂያው መቃረቡን ጠቅሰዋል ፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ የእርቅና የሰላም ማኅበር ሊቀመንበር ዶክተር ልኡልሰገድ አበበ በበኩላቸው በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ድጋፍ የሚያደርግበትን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ከቤቱ ሆኖ ክፍያ የሚፈጽምበት የኦንላይን እና የሞባይል መተግበሪያ ሥርዓት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር በላቸው ተስፋ የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ትብብር የህዳሴ ግድብ ድጋፍ ሰብሳቢ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡ ያለፈበትን የግንባታ ሂደቶች እና በአሁኑ ወቅት ግድቡ ያለበትን የግንባታ ደረጃ አስረድተዋል፡፡
ግድቡ የማንንም ጥቅም አይጎዳም ያሉት ዶክተር በላቸው ይልቁን የውኃ ፍሰቱን በማስተካከል የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ከማድረጉም በላይ ከኤሌክትሪክ ኀይል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የትስስር ሥርዓት የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ ወይዘሮ አማረች ክፍለማርያም እንደተናገሩት የሀገራችንን ህልውናን ለማስከበር መላው ኅብረተሰብ በአንድነት በተነሳበት በበርሚንግሃም እና ኮቨንተሪ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይህን ዘመቻ ከመደገፍ ጎን ለጎን የህዳሴ
ግድቡን ለማጠናቀቅ የገንዘብ ድጋፍ በተከታታይ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበርሚንገሃም እና ኮቨንተሪ የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ ይበልጥ በማደራጀት ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅሞች እና ከውጪና ከውስጥ ጠላቶቻችንን የሚፈጽሙብንን ሴራ በሕብረት ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ እንደሚሠሩ መግለጻቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ