ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ቡድኖችን ለማጥፋት በሚደረገው የህልውና ትግል ውስጥ የንግድ ሥርዓቱን የሚያዛቡ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

224
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዋጋ ንረትና በኢኮኖሚ አሻጥር፣ በሕገ ወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድ፣ በምርት ጥራትና ደኅንነትን በተመለከተ ከአስመጪዎች፣ አምራቾችና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።
በኢኮኖሚ ዘርፉ ባለድርሻ አካላት ወደ ጦርነት ግንባር ሳይሄዱ፣ ምሽግ ሳይቆፍሩ የጦርነቱ ተሳታፊ የሚሆኑበት መሆኑን የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገልጸዋል። “የእኛ ነፃነት በነፃ የተገኘ ሳይሆን ውድ ዋጋ የተከፈለበት ነው፤ በዘመናት ሂደት የገጠሙንን ፈተናዎች ያሸነፍነው በአንድነታችን ነው፤ እኛም ስለነገ ትውልድ ነፃነት መክፈል ያለብንን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነን” ብለዋል ሚኒስትሩ።
አቶ መላኩ በአስመጪነት፣ በአምራችነት የተሰማሩ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ ኢትዮጵያን ማጣትና ገንዘብ ማትረፍ ወይም ኢትዮጵያን ማዳንና አነስተኛ ትርፍ ማግኘት ምርጫ ላይ እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
“ከሁሉም ግን ሀገር ማዳንን እንደምታስቀድሙ እተማመናለሁ” ነው ያሉት።
በኢኮኖሚው ላይ ያለውን አሻጥር በመታገል ሕዝብን ማገልገል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡና ተናበው እንዲሠሩ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ቡድኖችን ለማጥፋት በሚደረገው የህልውና ትግል ውስጥ የንግድ ሥርዓቱን የሚያዛቡ ችግሮች ተከስተዋል። ኢኮኖሚያዊ ምክንያትን ያላገናዘበ የዋጋ ጭማሪ፣ ምርትን ያላግባብ ማከማቸት፣ ያለ ደረሰኝ ግብይት መፈፀም፣ የሸማች ማኅበራት በተቋቋሙለት ዓላማ መሰረት ያለመሥራት፣ የሕገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት፣ የቁጥጥርና እርምጃ ማነስ በንግድ ሥርዓቱ ላይ የተከሰቱ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያየዩ ምርቶች ያለቀረጥ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑንም አቶ መላኩ አንስተዋል። በቀጣይ የምርት አቅርቦትን ማሻሻል፣ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን፣ ቁጥጥርን ማጠናከር፣ በሕገወጦች ላይ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ በመንግሥት የሚተገበሩ ይሆናሉ ተብሏል። ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማቅረብ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ መሸጥ ፣ ያለበቂ ምክንያት ምርታማነትን አለመቀነስ ፣ የደላላ ጣልቃገብነትን ማስወገድና በደረሰኝ መሸጥ ከአምራቹና ከንግዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ኅላፊነት ነው ተብሏል።
ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ከጦርነቱ ቀድመው እንደሚለቀቁ የፕሮፖጋንዳ መረጃዎች በንግዱ ላይም “ገበያ ሊዘጋ ነው፣ ምርት ሊጠፋ ነው” የሚሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመልቀቅ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥሩ መኖራቸው በውይይቱ ተነስቷል። እነዚህን ችግሮች ከነምክንያታቸውና ውጤታቸው አይቶ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ ተነስቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ወቅቱ የምንጨካከንበት ሳይሆን እርስ በርስ ተዛዝነን የምናልፈው ነው ብለዋል። ጦርነቱ በላብ፣ በደምና በሕይወት እየተመከተ መሆኑን በማንሳት፡፡ ችግሩን በድል ለመወጣት በጋራ መቆም ግድ እንደሚል ተጠቅሷል። የሀገር ቀውስ ማንንም ስለማይመርጥ ፈተናውን በኅብረት በመቆም መወጣት ይገባል ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአውስትራሊያ ሜልቦርን የሚኖሩ የደሴ ከተማ እና አካባቢው ተወላጆች ለተፈናቃይ ወገኖች ከ330 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next article❝ሀገራችን የገጠማትን የህልውና ፈተናና የህዳሴ ግድባችንን በድል አጠናቀን የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን❞ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን