❝ጊዜው ያለንን ሁሉ ለህልውናችን ስንል የምናበረክትበት ነው❞ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

488

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ባወጡት መረጃ ❝ጊዜው ያለንን ሁሉ ለህልውናችን ስንል የምናበረክትበት ነው❞ ብለዋል።

አቶ ግዛቸው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያወጡት መረጃ ቀጥሎ ቀርቧል:-

ጊዜው ያለንን ሁሉ ለህልውናችን ስንል የምናበረክትበት ነው።

ይህ ጊዜ ያለምርጫችን ተገደን ራስን የማዳን ዘመቻ ውስጥ የገባንበት ግዜ ነው። ጠላቶቻችን ሰብዓዊነት የማይገዳቸው ለራሳቸው የቡድን ጥቅምና ለታሪካዊ የሀገራችን ጠላቶች ሲባል እንደ አማራ ሕዝብ እንድንጠፋ፤ እንደ ሀገርም እንድንበታተን በሸረቡት ተንኮል ህልውናችንን የማጥፋት አደገኛ ሴራ ውስጥ የገባንበት ግዜ ነው።

ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይታወቃል። በተደጋጋሚ የተጋለጠውም ይህ ሽብርተኛ ቡድን በስሙ ለሚቀልድበት የትግራይ ሕዝብ ጭምር የማይጠቅም፤ ወገኑ ከሆኑ ሌሎች የሀገሩ ሕዝቦች ጋር በማጋጨት የላኩትንና ለዓመታት ሲያዘጋጁት በነበሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች የተሰጠውን ተልዕኮ በትጋት እየፈጸመ የሚገኝ መሆኑ ነው።

ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች ህልውና አደገኛ እና ክፉ ጠላት ነው። ከጀርባው የሚደግፉትም ክፉዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከድህነት እንዳይወጣ በራሱ ሃብት እንዳይጠቀም ለዘመናት ሲሠሩ የነበሩ ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው።

ሽብርተኛው ቡድን አቅም ቢያገኝ ለዓለም ሕዝቦችም አደጋ እንደሆነ ይታወቃል። ከሌሎች ዓለም ዓቀፍ ሽብርተኞች ጋር አይተባበርም ብሎ አለማሰብ አይቻልም። መሰሎቹን ወይም ቢጤዎቹን ፍለጋም የሚችለውን ሁሉ እያደረገም ይገኛል።
እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከአሸባሪው ቡድን ጋር የምናደርገውን ፍልሚያ መልኩን እየለዋወጡ ያለባህሪው እንደ በጎ ለመታየት መሞከራቸውን ስንታዝብ፤ በስሙ ሽብርተኛ ብለው ላለመጥራት የሚግደረደሩበትና ለዋሳ አቋም መያዛቸውን ስንመለከት ፍትሕና ፍርድ እንዴት እየኮሰመኑ፣ እየቀጨጩ እንደሆነ ቁልጭ ብሎ የታየ ነጭ እውነት ነው።

ለራሳችን በቁርጠኝነት በጽናት መቆም ያለብንም ፍትሕና እውነት የተዛቡበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ነው። ለእኛ ለራሳችን ካልበቃን የምንተማመንበት የተሻለ ነገር እውነትን ከመድፈርና ከአንድነታችን በላይ ምርጫ የለም።

የተዛባ የዓለም ሁኔታ በመሬት ላይ ባለው እውነት ላይ ሳይሆን በተዛባ ዘገባና ሆን ብሎ በሚሠራ አሳሳች መረጃ ላይ የተመሰረተ የሚሆንበትን ብዙ አጋጣሚ ተመልክተናል። ይህ አካሄድም አሁን ብቻ ሳይሆን ሀገራችን በቅኝ ገዥዎች በተወረረች ጊዜም የታየ ክስተት ነው።

ያኔም ልክ እንዳሁኑ በጣም ጥቂት ወዳጆች ብቻ ነበሩን። አሁንም የምናየው ተመሳሳይ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንዲትን ታዳጊ ሀገር ራስዋን ከሽብርተኛ ለመከላከል በምታደርገው ትግል በጸረ -ሽብር ትግሉ አብሮ መቆም ባይፈልጉ ትግላችንን ባያደናቅፉ በበቃን ነበር።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸረ ሽብር ትግል ያደረገችውና እያደረገች ያለው ተግባር ተረስቶ በጸረሽብር ትግሉ ዋና ተዋናይ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ሀገሮች ሌላው ቢቀር ሽብርተኛን በስሙ መጥራት ለምን ከበዳቸው? ብለን ስናስብ መልሱ ከጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ ነው ቢባልም ከተለመደው የሀገሮች ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ሲገመገም የተለየ ገጽታም የሚያሳይበት ያልተለመደ ሁኔታ እናስተውላለን።

ይህ ያልተለመደ የሚሆነው ገጽታ ከአሸባሪው ትህነግ ባህሪም ጋር ይያያዛል። በስልጣን በቆየባቸው 30 ዓመታት የሠራቸው የማጭበርበር እና ጸረ- የሕዝቦች አንድነት ተግባር ውስጥ ለውስጥ ጊዜ ተወስዶባቸው የተከናወኑና የጥቂት ግለሰቦችን ልብና እዕምሮ በተለያየ መንገድ ሊይዝ መቻሉና አሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝቦች በዘረፈው ሃብት የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨትና ይህንንም የዕለት ኑሮአቸው ያደረጉ አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች በመያዙ በለመደው መረጃን የማዛበት ተግባር ለጊዜውም ቢሆን እየኖረበት ነው።

ይህ እውነትን የማዛባት (Disinformation) ተግባር እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብም ጭምር ለማሳሳት የቻለበት የተለመደ የሽብርተኞች ባህርይ የሚመነጭ ተግባር ነው። በውሸት ትርክትና በሐሰት ድል ብዙዎችን እያሳተ ኖሮአል።

እየታወቀበት ሲመጣ ደግሞ ሌሎች ትርክቶችን ይደርሳል። “ሕዝብን ነጻ ለማውጣት” በሚል ስም በሕዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር የማይሠራው ሰይጣናዊ ሥራ የለም። አልተሳካም እንጂ ኢትዮጵያን የመበታትን ዓላማው ይሳካል ብሎ የሚያስበው በዚህ መንገድ ነበር።

ሕዝባችን ግን ከዳር እስከዳር ከአሸባሪው ቡድን ፍላጎት ውጭ ዓለምን ባስደመመ ሁኔታ በአንድነት አሸባሪውን ለመመከትና ለመደምሰስ ተንቀሳቀሰ። ይህ የዓድዋን ታሪክ የደገመ ሁሉን አቀፍ ሀገር አድን ዘመቻ ወዳጅንም ጠላትንም ያስገረመ ሆኖአል።

በዚህ ሳንወድ በገባንበት ሀገርን የማዳን ዘመቻ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት መቆማችን ወሳኝ የድል መንገዳችን ነው። ይህን የሚገነዘቡ ጠላቶች የማይሞክሩት የመከፋፈል መንገድ የለም። ወዳጅ መስለውም በውስጣችን እየተንቀሳቀሱ አንድነታችንን ሊበትኑ ይሞክራሉ። እኛ ግን አንድነታችንን ከሚጎዳ በንግግርም በተግባርም ከሚገለጽ ማንኛውም ለጠላት ከሚመች እንቅስቃሴ መጠበቅ ይኖርብናል።

የአማራ ሕዝብ በአሸባሪው ቡድን በጠላትነት ተፈርጆ ህልውናው ፈተና ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት የአማራ ሕዝብ ሁሉም በሚችለው እየተረባረብ አስደማሚ ድል በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ይህን የድል ጉዞ አስጠብቆ ለማስቀጠል ሁሉም የአማራ ሕዝብ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ የመዋጋት አቅም ያለው በግንባር በመሰለፍ እውቀት ያለውም በእውቀቱ የሚችለውን ሁሉ የሚያደርግበት ጊዜ ነው።

አሁን ሕዝባችን እያሳየ ያለው ርብርብ አስደማሚ ነው። ለሽብር ቡድኑም መውጫ መግቢያ ያሳጣ የፍትሕና ራስን የመከላከል ትግል ነው።

ኢትዮጵያን አጠፋለሁ ብሎ ለተነሳው ለሽብርተኛው የትህነግ ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰጡት ምላሽ ሀገር በሽብርተኛ ቡድኑና በታሪካዊ ጠላቶቻችን እንደሚያስቡት በቀላሉ የምትጠፋ እንዳልሆነ አሳይቶአል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትብብር እና ሀገራቸውን ከጥፋት ለመታደግ ያሳዩት ወኔና እልህ ለጠላቶቻችን አስደንጋጭ ነው። ከአማራ ሕዝብ ጎን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመቆሙ ነገር ለእኛ ከፍ ያለ ድል ለጠላቶች ደግሞ ሞትና ያልጠበቁት ህመም ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አያውቁትምና ወዳጆቻቸውን ተማምነው ተሸወዱ።

ሽብርተኛ ሽብርተኛ ስለሆነ መጥፋት አለበት። በዚህ እልህ አስጨራሽ ጸረ-ሽብር ትግል ውስጥ መከተል ያለብን አካሄድ የሕዝቦችን አንድነት የሚያበረታቱና ጠላቶቻችን ከሚሰጡን ክፉ የቤት ሥራ ነቅተን የመጠበቅ አርበኝነትና ሰብዓዊ መርሆች የሚገዙን መሆን ይኖርብናል።

በመርህ ከሽብርተኞች የተለየን ነን። ሽብርተኛ ምን መርህ አለው?! በመርህ የተለየን ነን ስንል ሽብርተኛው በፕሮፖጋንዳም በተግባር ከሚፈጽመው ፈጽሞ የተለየን ነን ማለታችን ነው። ሽብርተኛው የአማራ ሕዝብ ጠላት እንደሆነ በአደባባይ ሳያፍር ባወጀው እና በተግባርም እንዳስመሰከረው ልናስብ አንችልም። አይደለንምም። የትግራይን ሕዝብ ጭምር ከአሸባሪው ቡድን የሚያላቅቅ ትግል ነው የአማራ ሕዝብ የጀመረው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሽብርተኛው ምግባር በተግባር ተቆጥተው በአንድ ላይ እንዲነሱ ያደረጋችውም የአሸባሪው ቡድን “ከአማራ ሕዝብ ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ” ማለቱን ተከትሎ “የለም የሚወራረድ ሂሳብም የለም እንጅ ካለም ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው” በማለት ሽብርተኛውን ቡድን ከትግራይም ሕዝብ ጫንቃ ለማውረድ ነው። ይህም በአጭር ጊዜ ተሳክቶ ኢትዮጵያ ከሽብርተኛ ቡድን ተላቃ ሙሉ አቅማችንን ወደ ልማት የምናዞርበት ጊዜ በደጅ ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በየቦታው በሀገር ውስጥም በውጭም የሚያደርጉት የአርበኝነት ተግባር የአጥፊውን ቡድን የተሳሳተ ስሌት ፉርሽ ያደረገ ሆኖ ተገኝቶአል። ተከፋፍለዋል ሲሉን አንድ ሆነን አገኙን። እንከፋፍላቸዋላን ብለው ሲሠሩም ያልጠበቁት አርበኝነትና አንድነት ሆነባቸው። ያልሞከሩት ክፉ ነገር የለም። በምድር ላይ ሊፈጸም የሚችል ተንኮል ሁሉ ተሞክሮአል። ተፈፅሟልም።
በምድር ላይ በሰዎች ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የማይታሰብ ከሰውነት ውጭ የሆነ አረመኒያዊ ተግባር ሁሉ ሽብርተኛው በገባበት ቦታና ተላላኪዎቹ ሰርገው በገቡበት ቦታዎች ሁሉ ሕዝባችንን ለሰቆቃ ዳርገውታል።

በምድር ላይ በሰው ታሪክ ከተፈጸመው ግፍ በላይ የሆነ ተፈጽሞአል። ይህንን ሁሉ ግፍ ግን ሽብርተኝነትን እንታገላለን የሚሉ ወገኖች እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሲያልፉት እየተመለከትን ነው።

በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ያሳስበናል የሚሉ ኀይሎች ነገር ከማወሳሰብ ይልቅ ቀላል መፍትሔው የጸረ – ሽብር ትግሉን መደገፍና ሽብርተኛውን ቡድን ለፍርድ በማቅረብ ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን የምናደርገውን ትግል መደገፍ አይቀልምን..???

በእውን ለሕዝብ ከታሰበ በአማራና በአፋር ክልሎች በንጹሐን ዜጎች ሽብርተኛው ቡድን ያደረሰው መከራስ እንዴት ነው እንዳልታየ የሚታለፈው? ለዚህ ነው ፍትሕና ፍርድ በተዛቡበት ዓለም ውስጥ ነን የምንለው። ስለዚህም ነው ከሽብር ሕዝባችንን ለመታደግ እና ሀገራችንን ከመጥፋት ለመታደግ ያለንን እና የምንችለውን ሁሉ በቁርጠኝነት ለማድረግ በየዘርፉ በአንድነት መቆም ያለብን።
ለዚህ ጊዜ ያልሆነ እውቀትም ገንዘብም ጉልበትም ለመቼ ሊሆን ነው?

ይህ ወቅት ከማንኛውም ግዜ በበለጠ ሁኔታ ህልውናችንን እና ሉዓላዊነታችንን ለማስጠበቅ ስንል ያለንን አቅም ሁሉ የምናበረክትበት ወቅት ነው።

ድል ለኢትዮጵያ!
ድል ለአማራ!!

Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሕልውና ዘመቻ ላይ ላሉ የመከላከያ ሠራዊትና ከየክልሉ ለተውጣጡ ልዩ ኀይሎችና በጦርነቱ ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች 800 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleበአውስትራሊያ ሜልቦርን የሚኖሩ የደሴ ከተማ እና አካባቢው ተወላጆች ለተፈናቃይ ወገኖች ከ330 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ድጋፍ አደረጉ፡፡