
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአጭር ጊዜ እንዲወገድ ባንኩ የሀገር ባለውለታነቱንና አለኝታነቱን አስጠብቆ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዚደንት አቤ ሳኖ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀገር ሰላም ስትሆን የልማት ፈርጥ ፣ ሀገር በወንበዴዎች ስትወረር ደግሞ የክፉ ቀን አለኝታ ሆኖ ዘመናት በዋጀ ጉዞው ሀገሪቱ ከተጋረጠባት ዘርፈ ብዙ ሴራ ለማሻገር ከሚረባረቡ ሀገር በቀል ተቋማት መካከል አንዱ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሀገር አለኝታና መከታ መሆኑን የሚናገሩት የባንኩ ፕሬዚደንት አቤ ሳኖ ባንኩ የሀገሪቱን ህልውና ለማስከበር ለተሰማሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ለአፋር ልዩ ኀይልና ዘመቻውን ለተቀላቀሉ ከየክልሉ ለተውጣጡ ልዩ ኀይሎችና ሚሊሻ አባላት እንዲሁም በጦርነቱ ለተጎዱ የኅብርተሰብ ክፍሎች ባንኩ 300 ሚሊዮን ፣ ከማኔጅመንትና ከሠራተኞች የተሰበሳበ ብር 500 ሚሊዮን በድምሩ 800 ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ የባንኩ ሠራተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ዘመቻውን ለመቀላቀል ለሚፈልጉ ሠራተኞች ሙሉ ጥቅማጥቅምና ደሞዝ ለቤተሰቦቻቸው ባንኩ ለመክፈል መወሰኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለው አሸባሪ ቡድን በአጭር ጊዜ እንደሚወገድ የባንኩ ጽኑ እምነት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱ ከያዘችው የልማት ጉዞ ወደኋላ ሳታፈገፍግ ዘመቻው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ልማቷ መመለስ ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- አየለ መስፍን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m