
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወልደትንሳኤ መኮንን አሸባሪው ትህነግ በዞኑ ያደረሰውን ጉዳት እና ሕዝቡ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ የዞኑ ሕዝብ በትግል ላይ እንደሚገኝ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
ከሐምሌ 5/2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አሸባሪው እና ወራሪው ትህነግ ቡድን በዞኑ ሕዝብ ላይ ግልጽ ወረራ ፈጽሟል።
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት የአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ዓላማ የአማራን ሕዝብ ማጎሳቆል እና ማዋረድ በመሆኑ በወረራቸው የዞኑ አካባቢዎች ላይ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል፡፡ በዚህም የመንግሥት እና የግለሰቦች ንብረት በተለይም ደግሞ በከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ ዘረፋ መፈጸሙን አንስተዋል፡፡ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ ማውደሙን ገልጸዋል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ በውኃ፣ በመብራት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በማድረሱ ማኅበረሰቡ በችግር ውስጥ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በጤና ተቋማት ላይ በፈጸመው ከፍተኛ ዘረፋ ተመላላሽ ታካሚዎች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሕጻናት አደጋ ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ከንብረት ዘረፋ እና ውድመት ባለፈ ዜጎችን ገድሏል፤ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር የቆየ ጥላቻውን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ከደረሰበት የአንበጣ ጉዳት ጋር ተዳምሮ ማኅበረሰቡ በችግር ውስጥ እንደሚገኝም ነው አቶ ወልደትንሳኤ የገለጹት፡፡
አሸባሪና ወራሪውን የትህነግ ቡድን እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ በሚደረገው ትግልም የአካባቢው ሕዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጎን በመሰለፍ ጀብዱ እየፈጸመ እንደሚገኝም ነግረውናል፡፡ በዚህም በራያ ቆቦ አካባቢ በሚገኙ ቀበሌዎች፣ በሃብሩ አካባቢ ሶዶማ፣ ድሬ ሎቃ፣ አረሪት፣ ህብሩ ሊጎ፣ ሮጋ መለዮ፣ ሊብሶ፣ ማህል አምባ እና ሌሎች አካባቢዎች ወጣቶች በመቀናጀት ጠላትን እየደመሰሱ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በመቄት ኮኪት አካባቢ አንድ አርሶ አደር 11 የጠላት ኀይልን መረፍረፉንም አንስተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በርካታ የጠላትን ኀይል እስከ ትጥቁ በመማረክ አካባቢያቸውን አለማስደፈራቸውንም ገልጸዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎችም ተቆራርጦ የገባውን የጠላት ቡድን ወጣቶች በመደራጀት መውጫ መግቢያ እያሳጡት እንደሚገኝ አቶ ወልደትንሳኤ አመላክተዋል፡፡ ከተጋድሎው ባለፈ አርሶ አደሩ ግንባር ለተሰለፈው የወገን ጦር የስንቅ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ወልደትንሳኤ የአሸባሪው ትህነግ አንዱ የጦርነት ስልቱ የሚያሰራጨው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የአሸባሪ ቡድኑን ወረራ ተከትሎ ❝ከአካባቢው ለቀው ወጥተዋል❞ በሚል የተሰራጨው ወሬ በአመራሩ እና በሕዝቡ መካከል ልዩነት በመፍጠር በተሟላ መንግድ ትግሉ እንዳይመራ የተለቀቀ አሉባልታ እና የተለመደ ፕሮፖጋንዳ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ወልደ ትንሳኤ በወቅቱ የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ የሥራ ስምሪት ለመስጠት ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመሆን እየሠሩ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚናፈሰው አሉባልታ አንዱ የአሸባሪው ትህነግ የተለመደ ፕሮፖጋንዳ መሆኑን አንስተዋል፡፡ እውነታው ግን አሁንም አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ተጋድሎ የዞንና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ማኅበረሰቡን የማደራጀት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
ማኅበረሰቡ ጠላትን በተቀናጀ መንገድ መመከት እንዳይቻልና ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ አሸባሪው ትህነግ ያልተያዘውን ቦታ እንደተያዘ አድርጎ በፎቶ ሾፕ እና በሰርጎ ገቦች በተነሳ ፎቶ በመልቀቅ የሽብር ተግባር እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ማንኛውንም መረጃዎች ማኅበረሰቡ ባለመቀበል እውነታውን ከትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑን በአጭር ጊዜ ለማስወገድ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m