
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወራሪው እና አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወረራ በፈጸመበት የሀራ ገበያ ከተማ አስተዳደር የንጹሐንን ሕይወት ቀጥፏል፤ ንብረት አውድሟል፤ ዝርፊያ ፈጽሟል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ 15 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት የሀብሩ ወረዳ ቁጥር 24 ቀበሌ ነዋሪ ታሪክ የማይረሳው ጀብድ ፈጽሟል፡፡
የሀራ ገበያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሐመድ አዲስ እንዳሉት ወራሪው እና አሸባሪው የትህነግ ቡድን በከተማ አስተዳደሩ የፈጸመው ጥፋት ቡድኑ በሕዝብ ላይ ያለውን ጥላቻ ማሳያ ነው፡፡ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፤ የግለሰቦች ንብረት ወድሟል ፤ ተዘርፏል ብለዋል፡፡ እናም ይህን አውዳሚ የሀገር እና የሕዝብ ጠላት በጋራ መደምሰስ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ወራሪው እና አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሚያሰራጨው የሐሰት ወሬ ሕዝቡ ሳይረበሽ አካባቢውን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የሀብሩ ወረዳ ቁጥር 24 ቀበሌ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ከአሸባሪ ቡድኑ ወራሪና ሰርጎገብ እየጠበቁ ይገኛሉ ነው ያሉት። ነዋሪዎቹ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኀይል ፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ጋር የሽብር ቡድኑን እየተፋለሙ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
ወራሪው እና አሸባሪው የትህነግ ቡድንን ለሚፋለሙ የጸጥታ አካላት አስተማማኝ ደጀን በመሆን ቡድኑን በአጭር ጊዜ መደምሰስ እንደሚገባ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ለነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንዲቀርብ ሁሉም እንዲረባረብም አቶ መሐመድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ